“ዘላቂ፣ አስተማማኝና ፍትሃዊ የስራ ዕድል በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግና እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል፤ በስራ ዕድል ፈጠራ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ዙሪያ በክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የተዘጋጀ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በክልሉ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የቤተሰብ ብልፅግናን አስቀድሞ ዕውን ማድረግ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ለቤተሰብ ብልፅግናችን ራዕይ ስኬት፤ ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ቀዳሚና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ዘላቂ፣ አስተማማኝና ፍትሃዊ የስራ ዕድል በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል አያይዘው አብራርተዋል።
የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ የዘርፉን የ2017 የሩብ ዓመት አፈፃፀም በጋራ በመገምገም፤ በቀጣይ አመራሩ በባለቤትነት መንፈስ እና በጊዜ የለኝም እሳቤ ለስራ ዕድል ፈጠራ ስኬታማነት የጋራ ርብርብ እንዲያደረግ ለማስቻል መሆኑንም ገልፀዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ በቅንጅት የሚሰራ የብዝሃ ሴክተር ስራ እንጂ በአንድ አካል ብቻ የሚከናወን አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮች፤ የዘርፉ ኃላፊዎች እና የተለያዩ ሴክተሮች በጊዜ የለኝም መንፈስ በጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ የሁሉም ቀዳሚ የጋራ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ተቀናጅቶ በመስራት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
አክለው፤ አመራሩ ስራዎችን ቆጥሮ በመስጠት እና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል አሰራር በመዘርጋትና አፈፃፀሙን በየጊዜው በመከታተል ለውጤታማነት መስራት ይገባዋል ብለዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ተግዳሮት የበዛበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እያንዳንዱን ተግዳሮቶ እንደ ግብዓት በመውሰድ ለቀጣይ ስኬት መፍጠሪያነት መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ብድርና መስሪያ ቦታን ጨምሮ፤ የተለያዩ ግብዓቶችን ለወጣቱ በማቅረብ እንዲሁም ያወቁና የበቁ እንዲሆኑ በክህሎት እና በችግር ፈቺ ድጋፍና ክትትል በማገዝ፤ ወጣቱን በስራ ዕድል ፈጠራ ራሱን ችሎ ለሌላው መትረፍ የሚችል አምራች ዜጋ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ፤ የግሉ ዘርፍ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ያሉንን ፀጋዎች በመጠቀም ባለፀጋዎች ለመሆን መስራት ይኖርብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ በክልሉ አርአያ የሚሆኑ የተለያዩ ስራ ዕድል በመፍጠር ስኬታማ የሆኑ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ልምድና ተሞክሮአቸውን በመቀመር ለሌሎች ማካፈል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ማጠቃለያ የስራ እድል ፈጠራ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል ቀጣይ አቅጣጫም አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም፡-
የስራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳ የሁሉም የጋራ ቁልፍ አጀንዳ ማድረግና ክፍተቶችን እየለዩ ዕቅዶችን በየወቅቱ እየከለሱ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይሄን ለማሳካት በገጠር አምስት ሄ/ርና በላይ፤ በከተማ ደግሞ አንድ ሄ/ር ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚውል የለማ መሬት ዝግጁ ማድረግ እና ጠንካራ ድጋፋዊ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ወጣቱን ወደ ስራ እንዲያስገቡ አመራሩ መደገፍና ማበረታታ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የስራ እድል ያለፈጠሩ ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዩንቨርሲቲዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን ለወጣቱ በመስጠት፤ ወጣቱን ለስራ ዝግጁ የሆነ፤ ትጉና ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል የበቃ የሰው ኃይል እንዲሆን ለማስቻል መስራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው፤ ወጣቱ፤ የመንግስት ሰራተኛው እና አመራሩ የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ የፈጠረውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም፤ የተሟላ የዲጂታል ክህሎት ጨብጦ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ስልጠናውን ተመዝግቦ መከታተል እንዲሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለዚህም አመራሩ በየአካባቢው ወጣቱን በመቀስቀስ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እስከ ጥቅምት 30 በስራ ዕድል ጠፈራ ላይ ትኩረት ያደረጉ የንቅናቄ መድረኮች እንዲዘጋጁ የስራ ስምሪት የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አመራሩ የስራ ዕድል ፈጠራን የጋራ አጀንዳው በማድረግ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎችን በቅንጅት በመስራት ዘርፉን በቁርጠኝነት መምራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና የስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ በበኩላቸው በሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል የስራ አጥነት ችግር ዋነኛው መሆኑን ጠቀሰው፤ ችግሩን ለመፍታት ተገቢውን አመራር መስጠትና ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ለዜጎች ዳቦ ከማቅረብ በዘለለ የሀገር ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ጤነኝነት መገለጫ እና የሰው ተኮር እሳቤያችን ማረጋገጫ ነዉ ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገራችን የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ እንደመከተሏ በ 5ቱም ዘርፎች ኢንተርፕራይዞችን በስፋት በማሰማራት ማሳደግ እና የሀገር ግንባታ አካል አድርጎ መዉሰድ እንደሚገባ ም/ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ገልፀዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 63 ተኪ እና 8 ወደ ዉጪ የምላኩ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ከመሬት፣ ብድርና ሼድ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ ዘላቂ የስራ ዕድል በመፍጠር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግናዉ የተረጋገጠ ክልልን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።