“የተደራጀ ቅንጅታዊ አሰራርን በቋሚነት በመዘርጋት የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታትና የህዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ መስራት ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
በክልሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ተደራሽነት እና አስተዳደር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደው የምክክር መድረክ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከመሰረተ ልማት አቅርቦት፤ ተደራሽነት እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች ለረዥም ጊዜ የቆዩና ፈርጀ ብዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ የፕሮጀክቶች ከፍተኛ የጥራት ችግር እና በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ከፍተኛ የጊዜና የሀብት ብክነት ሲያስከትል መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም ክልሉን ለተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ ሲዳርግ ከመቆየቱም በላይ ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ እንግልት በመዳረግ በክልሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ስርጭት ላይ የኢፍታሀዊነት ጥያቄ እስከማስነሳት የደረሰ ችግር ማስከተሉን አብራርተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ አያይዘው በክልሉ በዞኖችና በታችኛው መዋቅር ከፍተኛ የሆነ የአሴት አስተዳደር ችግር መኖሩንም ገልጸው ይህም የመሰረተ ልማት ችግሩን ያሰፋው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነት በፌዴራል መንግስቱ በከፍተኛ ወጪ የሚሰሩ የመንገድ፤ የመብራት እና የቴሌኮሚ መሰረተ ልማቶች ሳይመረቁ ለጥገና የመዳረግ፤ ተገቢውን ግልጋሎት ሳይሰጡ ለስርቆት፤ ብልሽት እና ውድመት መጋለጥ ችግሩን ይበልጥ ያባባሰው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የችግሩን ጥልቀት በማጠን ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፤ ስርጭት፤ ጥራትና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተደራጀ አግባብ በተቋማዊ ማዕቀፍ ለመፍታት በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ክልሉ የከተማና የገጠር መሰረተ ልማት ጉዳዮችን ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም በባለቤትነት የሚከታተልና የሚመራ ተቋም በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ስር ማቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡
ይህም በተቋማዊ ማዕቀፍ በአሰራር የተደገፈ ፕሮጀክቶችን መሰረት ያደረገ ቀጥተኛ ግንኙነትን በየደረጃው ካሉ መዋቅሮችና ተቋማት ጋር በመዘርጋት በተቀናጀ እና በተደራጀ አግባብ ተጋግዞ ችግሩን መፍታት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪ ዞኖችን በክላስተር በማቀናጀትና ፕሮጀክቶችን መሰረት ያደረጉ ውይይቶችን በየጊዜው በማካሄድ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋት የሚገባ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከአሴት አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በፍጥነት በማረም ነባርና አዲስ የመንገድ፤ የመብራት፤ የቴሌኮሚ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት መከታተል፤ መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በተደራጀ ቅንጅታዊ አስራር የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት የህዝባችንን የልማት ጥያቄ በብቃት ለመመለስ መስራት ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፤ የዞን አመራሮች፤ የተቋማት ሃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡