ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን፤ የደቡብ ምዕራብ ቀጠና ቃለህይወት ቤተክርስትያን በጋሞ ዞን በማከናወን ላይ ያሉ የልማት ስራዎች ጎብኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው የቤተክርስቲያኗን የትምህርት ዘርፍ የስራ እንቅስቃሴ በአርባ ምንጭ ከተማ የተመለከቱ ሲሆን፤ ለትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ፤ ተሳትፎ እና ቅንጅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡
ጉብኝቱ የክልሉ መንግስት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን በገመገመበት ማግስት የተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሩብ ዓመቱ ክልሉ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በርካታ አመርቂ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በግምገማው በጥንካሬ የተለዩትን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ፤ እንደ ክፍተት ለተለዩ ትኩረት ሰጥቶ ውጤታማ ስራ ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውሰዋል፡፡
ጉብኝቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መነሾ የተደረገ መሆኑንም ገልፀው፤ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት የሆነው ትምህርት፤ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ትምህርት የዕድገትና የብልፅግና መሠረት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጉብኝቱ ለዘርፉ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያለውን አስትዋጽኦ ለማየትና የትምህርት ስራን ለማጠናከር የሚረዳ ተሞክሮ ለመቀስም ያለመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በጉብኝቱ የደቡብ ምዕራብ ቀጠና ቃለህይወት ቤተክርስቲያን በአርባ ምንጭ ከተማ ከቅድመ መደበኛ አስከ 12ኛ ክፍል ሞዴል መሆን የሚችል ትምህርት ቤት በማቋቋም፤ ከ1 ሺህ 4 መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የትምህርት ቤቱ የቅድመ መደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ዘመናዊ፤ የተደራጀና ውጤታማ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህፃናትን የሚይዙበት እና ትውልድ የሚቀርጹበት መንገድ ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ፤ ተቋሙ ተማሪዎቻቸውን በብሔራዊ ፈተና ሙሉ በሙሉ ማሳለፍ ከቻሉ ተቋማት አንዱ መሆኑን ያደነቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተቋሙን የትምህርት አስተዳደር ስርዓትና ለውጤት የበቁበትን አግባብ አጢኖ ተሞክሮ በመውሰድ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ለማስፋት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ ተቋሙ ባለው ሀብት የተማሪውንና ሌሎች ስራ አጥ ወጣቶች ዝንባሌ እና ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚሰጣቸው የሙያ ስልጠናዎች፤ በተለይ ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ዘጎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ በማስገባት፣ ምርታማ በማድረጉ ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ስራን ውጤታማነት ለማረጋገጥ መንግስት ብቻውን የሚያደርገው ጥረት ብዙም ውጤታማ አይሆንም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጉብኝቱ ከባለድርሻ አካላት ተሞክሮ መውሰድ ብቻ ሳይሆን፤ ተቀናጅቶ አብሮ የመስራት አስፈላጊነት ግብዓት የተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ እንደ ሀገር የገጠመን የትምህርት ስብራት ለመጠገን በሚደረገው ጥረት፤ የክልሉን የትምህርት ዘርፍ ለማጠናከርና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ከመሰል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ በጋራ የሚሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡
ከትምህርት ስራ ውጪ፤ ቤተክርስቲያኗ ከ2 ሺህ በላይ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን የመደገፍ እንዲሁም ኤች አይ ቪ በደማቸው የተገኝባቸው ግለሰቦች የህክምና ክትትል እንዲገኙ የማድረግና የመደገፍ የበጎ አድራጎት ስራ በመስራት ላይ መሆኗም በጉብኝቱ ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪ ቤተክርስትያኗ የቁጠባ ባህልን የሚያጠናክር የፋይናንስ ስረዓት በመዘርጋት፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ሲሆን፤ በአነስተኛ ዋጋ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የሙያ ስልጠናዎችም በመስጠት ላይ ትገኛለች።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቤተክርስቲያኗ በማከናወን ላይ በሚትገኘው ሰው ተኮር ተግባር መደሰታቸውን ገልፀው፤ ተግባሩ ሊበረታታ የሚገባው እና ለሎች ሞዴል ሊሆን የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በቀጣይ ቤተክርስትያኗ በማከናወን ላይ ያለችውን የልማት ስራዎች ከጋሞ ዞን እና ከከተማው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ማጠናከርና ተደራሽነቱን ለማስፋት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።