
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዪ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።



መስተዳድር ምክር ቤቱ በ20ኛ መደበኛ ስብሰባው፡- ለም/ቤቱ የቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች፤ መመሪያዎች እና የውሳኔ ሀሳቦችን መርምሮ ማፅደቅ፣ በክልሉ የማዕድን ልማት ዘርፍ ዙሪያ በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጥን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ ውሳኔ የሚሹ ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች፤ መመሪያዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች ላይ ሲሆን፡-
የኢንቨስትመንት አስተዳደርን ለማስፈፀም የወጣ ደንብ፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ ሲለቀቅ የሚከፈል ካሳ እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ የወጣ መመሪያ እንዲሁም በክልሉ ማዕከላት የሚገነቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህንፃ ግንባታ በተመለከተ የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ በዝርዝር በመወያያት ውሳኔ አሳልፏል።



ምክር ቤቱ በቀረቡ ረቂቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ከነማሻሻያቸው አፅድቋል፡፡
ምክር ቤቱ በተያያዘ በክልሉ ማዕከላት የሚገነቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህንፃ ግንባታ በተመለከተ በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ በመወያየት አቅጠጫ አስቀምጧል፡፡




መስተዳድር ምክር ቤቱ በሁለተኛ አጀንዳው የክልሉን የማዕድን ልማት ዘርፍ ስራዎች በተመለከተ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ክልሉ በማዕድን ልማት ዘርፍ በርካታ የከርሰ ምድር ፀጋዎችና እምቅ የመልማት አቅም ያለው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በዘርፉ በተሰሩ ስራዎች የተሻለ መነቃቃት መኖሩ ተመልክቷል፡፡
ምክር ቤቱ በውይይቱ በክልሉ የማዕድን ልማት ዘርፍ ያሉ አበረታች ስራዎችን አጠናክሮ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍና ክልሉ ባለው እምቅ አቅም ልክ በማልማት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ቀጣይ አጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።