የክልሉ መንግስት ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 455 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት የይቅርታ አዋጁን መስፈርት ላሟሉ 1 ሺህ 455 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር ያሳዩ እና በሕግ በተደነገገው የይቅርታ መስፈርትን ማሟላታቸው በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው።

በዚሁ መሰረት የይቅርታው ተጠቃሚዎች ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የቆዩ፤ በጤና ችግር፤ በዕድሜ መግፋትና ከሕጻናት ጋር አብረዉ የታሰሩ እንዲሁም ከተፈረደባቸው አንድ ሦሥተኛ እና ከግማሽ በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ይቅርታው ከተደረገላቸው 1 ሺህ 455 የህግ ታራሚዎች መካከል1 ሺህ 435ቱ ከእስር የሚፈቱ ሲሆን ቀሪ 20 ታራሚዎች የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ገልጸዋል።

የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የህግ ታራሚዎች መካከል 95ቱ ሴቶች ሲሆኑ 1 ሺህ 360ው ወንዶች መሆናቸውንም አመልክተዋል

ርዕሰ መስተዳድሩ የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የህግ ታራሚዎች የይቅርታን እሴት ተላብሰው ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን በተለያዩ የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ህብረተሰቡም በይቅርታ የተለቀቁት የህግ ታራሚዎች በፈፀሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ ታርመው የወጡ መሆኑን በመረዳት መልካምና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply