ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በድጋሚ ገልፀው ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
አደጋው በስፍራው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ መንግሥት የአፋጣኝ የነፍስ አድን ስራና የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይም የክልሉ መንግስት የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ስራን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊትም በአካባቢው የዝናብ ወቅት የጎርፍ አደጋ የመድረስ ሁኔታዎች በመኖራቸው የክልሉ መንግስት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ሁለት ቤተሰቦች ሙሉ በሙሉ በናዳ በመዋጣቸዉ እነሱን ለመታደግ በወጣው ቁጥሩ ከፍ ያለ ህዝብ ላይ ያልተጠበቀ ናዳ መጥቶ የዜጎችን ህይወት መቅጠፉን አስረድተዋል።
በደረሰው ከፍተኛ አደጋ እስከአሁን በተደረገዉ ፍለጋ የ232 ወገኖች ህይወት መጥፋቱን ገልፀው 10 ሰዎች በህይወት ተገኝተው የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው በመልካም ሁነታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት በዘላቂነት ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ ከፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸው እስከአሁን በተደረገው ድጋፍ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና 16 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተፈጠረው አደጋ ከ5 መቶ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከ 6 ሺ በላይ ዜጎች የመሬት ናዳ ሊደርስ በሚችልበት ተጋላጭ ቦታ ላይ በመሆናቸው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ አደጋ አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቋሞ በመስራት ላይ ሙኑን ተናግረዋል።
በደረሰው አደጋ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የክልል መንግስታት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአከባቢው ማህበረሰብ፣ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና አለም አቀፍ መንግስታት በማድረግ ላይ ስላሉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።