ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖቻችንን በቦታው ተገኝተው ሀዘናቸውን በመካፈልና በማጽናናት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አስከፊ ጉዳት ቦታው ላይ ተገኝቼ ወገኖቼን ማፅናናት አለብኝ ብለው በመምጣታቸው በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የደረሰው ድንገተኛ አደጋ በወገኖቻችን ላይ ያስከተለው ጉዳት እጅግ ልብ ሰባሪና መቋቋም ከምንችለው በላይ ለጽኑ ሀዘን የዳረገን ነውም ብለዋል፡፡
አክለውም አደጋው እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ቤት የተዘጋበት፣ እስካሁን ይመጣሉ እያሉ የሚጠብቁ ህፃናት ብቻቸውን ያለ ወላጅ የቀሩበት፤ እናቶችንና አረጋዊያንን ያጣንበት ጽኑ ሀዘን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህ አስከፊ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ነፍስ ፈጣሪ በአፀደ ገነት ያኑሪልን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ወገኖች መፅናናትን ተመኝተዋል።
የክልሉ መንግስት አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ ከአካባቢው ማህበረሰብ፤ ከዞኑ አስተዳደር፤ ከፌዴራል ተቋማት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አፋጣኝ የነፍስ አድንና የሰብዓዊ ዕርዳታ ምላሾች በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረው በቀጣይም የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር ሁሉአቀፍ ድጋፍች የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ ከአጭር ጊዜ አፋጣኝ የነፍስ አድንና የሰብዓዊ ዕርዳታ ምላሾች ጎን ለጎን በአደጋው የተጎዱ ወገኖችንና በአካባቢው የአደጋ ተጋላጮችን ከአደጋ ስጋት ነፃ በሆነ አግባብ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ክልሉ ከህዝቡ፤ ከፌዴራል መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ርብርብ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ስራውን በተደራጀ አግባብ የሚመራ ክልላዊ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱንም አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የአደጋው ልብ ሰባሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋውን ተከትሎ መላ ኢትዮጲያዊያን፤ የፌዴራል መንግስት፤ ክልሎች፤ አጋር ተቋማትና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ ጭምር ያሳዩት ወገንተኝነት የሚያበረታና ከአደጋው ለተረፉ ወገኖችም ተስፋን የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በየደረጃው በአይነት እና በገንዘብ እየተደረጉ ላሉ ድጋፎች በክልሉ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በቋሚነት እስከምቋቋሙ የተጀመሩ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከአደራ ጭምር ጠይቀዋል፡፡
በተለይ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለተጎጂዎች ለማቅረብ በየአካባቢው የተጀመሩ ወንድማማችነትን የሚያጠነክሩና በጎነትን የሚያፀኑ ሀብት የማሰባሰብ ተግባራትን የበለጠ በማጠናከር አስፈላጊ ድጋፎችን ለአደጋው ሰለባዎች በአፋጣኝ ማድረስ ይገባል ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡