የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ምክር ቤት የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2017 ጠቋሚ ዕቅድ ተወያይቶ አፅደቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤው ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባቀረቡት የክልሉ መንግስት የ2016 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።  

በውይይቱ ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የክልሉ መንግስት የ2016 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ ከምክር ቤት አባላቱ የተለያዩ ጥያቆዎች የተነሱ ሲሆን በርዕሰ መስተዳድሩ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀረበው የክልሉ መንግሰት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በስፋት በመወያት ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመቀጠል የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት አመት ጠቋሚ ዕቅድ ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፤ የምክር ቤት አባላቱ ጠቋሚ ዕቅዱን በተመለከተ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበው በርዕሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጠቋሚ ዕቅዱን ባቀረቡበት ወቅት የክልሉ መንግስት በ2016 በጀት አመት ህዝቡን በማስተባበር የክልሉን ዘላቂ ሰላም፤ ልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት መሰረት የጣሉ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረው በ2017 ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ በየዘርፉ የተጀመሩ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎና በአመራሩ ቁርጠኝነት ከዳር በማድረስ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ የሚደረግ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

በተለይ የክልሉን የውስጥ የገቢ አቅም በማሳደግና ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ተጠቅሞ ተጨማሪ ሀብት በመፍጠር የክልሉን ኢኮኖሚ ለማጎልበት እና የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ እንዲሁም ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ምርታማነትን በላቀ ደረጃ በማሳደግ የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥና ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ምርታማነት የሚደረገው ሽግግርን ባጭር ጊዜ ዕውን ለማድረግ የሚሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

በ2017 በጀት አመት ክልሉ ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል የውስጥ ገቢ አቅምን በማሳደግ 75 በመቶ የወጪ ፍላጎትን በራስ አቅም መሸፈን እና በክልሉ የሰፈነን አንጻራዊ ሰላም በማጽናት የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ የሚገኝበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው የክልሉ መንግስት የ2017 ጠቋሚ ዕቅድ ላይ በጥልቀት በመመከር በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

Leave a Reply