
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለ129ኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
እንኳን ለ129ኛው የአድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ቀን በሰላም አደረሰን! አደረሳችሁ!
አድዋ መላው ኢትዮጵያዊያን ስለ ሀገር ክብርና ሉዓላዊነት በላቀ የሀገር ፍቅር፤ በቃላት የማይገልጽ ወኔ እና ጀግንነት ከጫፍ ጫፍ በመትመም ባሕር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ዘመናዊ ትጥቅ ታጥቆ በጉልበተ ተማምኖ የመጣን ወራሪ ኃይል በአንድነት ድል ያደረጉበት የጋራ አኩሪ ታሪካችን፤ የብሔራዊ ክብራችን ዓርማ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል የሆነው የአድዋ ድል፤ የአልሸነፍ ባይነት መንፈስን አጎናፅፎ የመብትና የሉዓላዊነት ትግልን ያቀጣጠለ የመላው ጥቁር ህዝቦች የጋራ ታሪክም ነው፡፡
ከዚህም በላይ አድዋ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን የኅብረት፤ የኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የአሸናፊነት ምልክት ነው፡፡ ጀግኖች አባቶቻችን ከልዩነት ባሻገር በአንዲት ኢትዮጵያ ጥላ ስር በኅብረት በመቆም ባደረጉት ተጋድሎ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማይሻር የአሸናፊነት ማህተም ያተሙበት አንጸባራቂ ድል፡፡
አድዋ ከአካባቢያዊ ፍላጎት በላይ ለላቀ የጋራ ሀገራዊ ትልም በአንድ ልብና መንፈስ በመሰለፍ በትብብር ሁሉን አሸናፊና ሁሉን ተጠቃሚ ለሚያደርግ፤ ዘመን ተሻጋሪና ትውልድ አሻጋሪ ድል መብቃት እንደምንችል ያስተማረን አኩሪ የታሪካችን ክፋይ ነው፡፡

የዛሬውም ትውልድ የአንድነትንና የኅብረትን ኃያልነትና ሪትዕነት ከጀግኖች አባቶቻችን በመማር፤ ከነጠላ ከፋፋይ ትርክቶች ይልቅ በገዥ የብሔራዊነት ትርክት ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማፅናት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የራሱን አሻራ ሊያኖር ይገባል፡፡
ጀግኖች አያት ቅደመ አያቶቻችን በፈተናዎች ፀንተው፤ ባደረጉት የአልሸነፍ ባይነት ተጋድሎ ያጎናፀፉን በዘመን የማይደበዝዝ አንፀባራቂው የአድዋ ድል፤ የፅናትና የአልበገር ባይነት ተምሳሌት ነው፡፡
ድሉን ሲንዘክር፤ ከቀደሙ አያት ቅደመ አያቶቻችን ሀገርን በልዩነት ውስጥ የማፅናት ጥበብ፤ ሀገርን በችግሮች ውስጥ የማሻገርን ፅናት ትምህርት በመውሰድ ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡
ከዚህም ባለፈ አድዋ ታላቅ ብሔራዊ ድልና ብሔራዊ ኩራት ብቻ ሳይሆን ታላቅ ኃላፊነት መሆኑንም መገንዘብ ያሻል፡፡ ከድሉ ጋር የአድዋ ጀግኖች አርበኞች የሀገርን ክብር፤ ሉዓላዊነትና ነፃነት የመጠበቅ እና የታፈረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን የማሻገር ታላቅ ኃላፊነት አስረክበውናል፡፡
በመሆኑም ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረን የሀገራችንን ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት በማረጋገጥ ሉዓላዊነቷ በሙላት የተከበረ፤ የታፈረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማውረስ ይጠበቅብናል፡፡
የይቻላል መንፈስና የአርበኝነት ስነልቦናን ያወረሰን የአድዋ ድል የትናንት ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ህያዊ የአሸናፊነት ታሪካችን በመሆኑም፤ ከመቸውም ጊዜ በላይ ድህነትንና ተረጂነትን ታሪክ በማድረግ ድሉን ለመድገም በቁጭት መነሳት ይኖርብናል፡፡
ለዚህም የዳግማዊ አድዋ ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድባችንን ከዳር ለማድረስ ከመረባረብ ባለፈ እንደ ሀገር የጀመርናቸው ዘርፈ ብዙ የልማት፤ ምርታማነትን የማሳደግና ብልፅግናን የማረጋገጥ ጥረቶች በማፅናት፤ ለሀገራዊ የልማትና የብልፅግና ራዕይ ስኬት በጋራ ልንተጋ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ስለ ሀገር ክብርና ልዕልና ዋጋ የመክፈል ተምሳሌት የሆነው የአድዋን ድል መታሰቢያ ሲንዘክር፤ በየተሰማሩበት የሥራና የሞያ መስክ ሀገርን በማስቀደም፤ ለሀገር ክብር፤ ሉዓላዊነት፤ ሰላም፤ ዕድገትና ልማት ዋጋ ለከፈሉ እና እየከፈሉ ላሉ ሁሉ ምስጋናና ዕውቅና በመስጠት ሊሆን ይገባል፡፡
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ!!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!