የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ15ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በአርባምንጭ ከተማ ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባው ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በመታየት ላይ ባለው ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ፤ በክልሉ የአደጋ ስጋት ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በተለያዩ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦች ላይ በጥልቀት በመመከርና በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በቅርቡ ከተደረገው ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በክልሉ እየተያ ያለን ምንም ዓይነት የገበያ መሰረት የሌለው ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪን የተመለከተ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በውይይቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በተለይ የተለያዩ መሠረታዊ ሸቀጦችን በመሸሸግና የገበያ ዕጥረት ያለ በማስመሰል ያልተገባ ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ የማድረግ እና ኅብረተሰቡን ለብዝበዛ የመዳረግ ሁኔታዎች በመታየት ላይ መሆናቸውን ገምግሟል፡፡

ለዚህም በህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት የንግድና የገበያ ስርዓቱን በሚያዛቡ አካላት ላይ በቅንጅታዊ አሰራር የታገዘ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የማስተካከያ ህጋዊ እርማጃዎች በመወሰድ ኅብረተሰቡን ካልተገባ ብዝበዛ ለመታደግ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀመጧል፡፡  

መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በክልሉ ከክረምቱ የዝናብ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና የአደጋ ስጋት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በመነጋገር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይ በክልሉ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ሲሰራ ቢቆይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በመጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ የመጣል ሁኔታ መኖሩና ከዚህ ጋር ተያይዞ የናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመደገፍ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ መክሯል፡፡

በተጨማሪ ምክር ቤቱ በክልሉ አደጋ ስጋት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በመነጋገር በተለይ የአደጋ ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩ የክልሉ አካባቢዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ የተጀመሩ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት ኅብረተሰቡን በማንቃትና በንቃት በማሳተፍ ማጠናከር የሚቻልበትን አቅጣጫም አስቀምጧል፡፡

የክልሉን አደጋ ስጋት ስራ አመራር አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት አቅም ማጎልበት እንደሚገባም በውይይቱ ተዳሷል፡፡

በተያያዘም በክልሉ የተጀመሩ የተራራ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን ጨምሮ የተፈጥሮ ጥበቃና እንክብካቤ ስራውን ማጠናከር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቁልፍ መሆኑም በስብሰባው ተመላክቷል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል የተወያየው በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦች ላይ ሲሆን፤ እነዚህም፡-

  • የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ አዋጅ፣
  • የሰንደቅ አላማ አዋጅ፤
  • የፓሊስ አባላት መተዳደሪያ ደንብ እና የታራሚዎች ደንብ ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቀረቡ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው ያፀደቀ ሲሆን፤ አዋጆችን ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል፡፡

በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ የክልል ማዕከላትና ሴክተር ቢሮዎች የበጀት ድልድል እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በመወሰንና ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

Leave a Reply