የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በ16ኛ መደበኛ ስብሰባው የክረምት ስራዎች አፈፃፀም ጨምሮ በተለያዩ ረቂቅ ደንቦች እና ሌሎች ተያያዥ የካቢኔ ውሳኔ የሚሹ ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በክረምት የታቀዱ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስራዎች በተመለከተ ባደረገው ውይይት በደቡብ ኦሞ ዞን፤ በዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሀይቅ ሙላት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች አስቸኳይ ምላሽ መስጠት እና የጎፋ ዞን ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም በተመለከተ ተወያይቷል።
በዳሰነች ወረዳ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የቅድመ መከላከል፣ የፈጥኖ ደራሽ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ ማሽኖች በመጠቀም ውሃ የማፍሰስና ግድቦችን በመስራት መስመር የማስቀየስ እንዲሁም ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸው ተመልክቷል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ የአደጋውን ጉዳት መጠን ለመቀነስ እና ለተፈናቃዮች ተገቢውን የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረጉ ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር፤ የተዋቀረው የአደጋ ምላሽ ሰጪ ግብረሃይል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲረባረብ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በጎፋ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋሙ ስራ ያለበት ደረጃም በምክር ቤቱ ተገምግሟል፡፡
በዚህ ረገድ ለተጎጂዎች በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበውን ድጋፍ በመጠቀም የቤት ግንባታና ሌሎች አስፈላጊ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት በተቀናጀ አግባብ በፍጥነት የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የክረምት ስራዎች አፈጻጸም፡- የትምህርት ቤቶች የ2017 የትምህርት ዝግጅት፣ የክሬምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች፣ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ፣ የኑሮ ውድነትና ገበያ ማረጋጋት፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የገቢ አሰባሰብ እንዲሁም የሰላምና ፀጥታ ስራዎች በተመለከተም ተወያይቷል፡፡
በውይይቱም በህዝብ ተሳትፎ በንቅናቄ በተሰሩ የክሬምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች በተለይ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳትና ግንባታ፣ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ተከላ፤ የደረጃ ሐ ግብር አሰባሰብ እና ሌሎችም ውጤታማ ስራ መሰራቱ ተመልክቷል፡፡
ምክር ቤቱ በተያያዘ በቀሪ ጊዜያት መከናወን የሚገባቸው እና በ2017 በልዩ ትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ስራዎች በመለየት የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ የሚደረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ፤ በተለይ መጪው በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሆን ተብሎ የሚፈጠር ዕጥረትና የዋጋ ንረት ለመከላከል፤ ገበያን የማረጋጋትና ምርት ወደ ገበያ ከማቅረብ አንፃር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተገልጿል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በዝርዝር የተወያየው በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች ላይ ሲሆን፡-
ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት ድጋፍ አሰጣጥ የተመለከተ ደንብ፤ የከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ደንብ፣ የአቃቤ ህግ መተዳደሪያ ደንብ እና የታራሚዎች መኖ በተመለከ በተዘጋጀ የጥናት ሀሳብ ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው አፅድቋል።
በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ የካቢኒ ውሳኔ በሚሹ ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።