የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት፤ ዛሬ በበይነ መረብ ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዪ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በ18ኛ መደበኛ ስብሰባው በመንግስት ሰራተኞች የደምወዝ ማሻሻያ መመሪያ፣ የልማት ተነሺዎች ምትክ መሬት ማስተላለፍ፣ 19ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አከባበር እንዲሁም ሌሎች የካቢኔ ውሳኔ በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡
ምክር ቤቱ በመጀመሪያ በመንግስት ሰራተኞች የደምወዝ ጭማሪ አፈጻጸም መመሪያ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ፤ ካለፍው የጥቅምት ወር ጀምሮ የደምወዝ ጭማሪው ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የልማት ተነሺዎችን ምትክ ቦታ ማስተላለፍ በተመለከተ አጀንዳው፤ በከተማ መልሶ ማልማት ምክንያት ተነሺ የሆኑ ግለሰቦች ምትክ ቦታ ወይም የመንግስት ቤት አዘጋጅቶ መስጠት ተገቢ እና ህጋዊ መሆኑን የጋራ መግባበት ላይ በመድረስ የቀረበውን አጀንዳ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
ምክር ቤቱ በክልሉ አዘጋጅነት የሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ዝግጅትን የገመገመ ሲሆን፤ ዝግጅቱ በዓሉን በይዘትም ሆነ በድምቀት ከፍ ባለ ደረጃና የክልሉን ገፅታ በሚያጎላ መልኩ ለማክበር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ በቀሪ ጊዜያት በዓሉ በታላቅ ድምቀት ለማክበር እንዲቻል መስተዳድር ምክር ቤቱ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ በማሳሳብ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
ከዚሀ በተጨማሪ መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቋል።