ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በሳውላ ማዕከል ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዪ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በ19ኛ መደበኛ ስብሰባው፡- የክልሉን መንግስት የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች፣ የቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች እና አዋጆችን መርምሮ ማፅደቅን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ ውሳኔ የሚሹ ተያያዥ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በክልሉ መንግስት የ2017 የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ሲሆን፤ የክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት የስድስት ወር አፈፃፀም ሪፖርት የዳሰሰ ሰነድ ቀርቦ ከተያዘው ግብ አንፃር ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እና ክፍተቶችን ለይቶ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱ በግማሽ ዓመቱ በክልሉ የማስፈፀም አቅምን ከፍ የሚያደርጉ ቁልፍ ግቦችን በማስቀመጥ፣ አቅምን ያገናዘበ ዕቅድ እና የፈፃሚ ዝግጅቶችን አድርጎ ወደ ተልዕኮ በመግባት አመርቂ ስራዎች መሰራታቸው ተገምግሟል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለሙ ዘርፈ ብዙ የሰላምና ፀጥታ፤ የልማት እና መልካም አስተዳደር ስራዎች መስራተቸው ተመልከቷል፡፡
በውይይቱ በተለይ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ፤ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በመደረግ ላይ ባሉ ጥረቶች፤ በከተሞች በህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ በመከናወን ላይ ባሉ የኮርደር ልማት ስራዎች፤ በኢንቨስትመንት፤ በገቢ አሰባሰብ እና ሌሎችም አበረታች ውጤት መመዝገቡ ታይቷል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ በቀጣይም:- የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፤ የሌማት ቱሩፋት፣ የዋጋ ንረት ቁጥጥርና ክትትል፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት፣ የትምህርትና የጤናው ዘርፍ ስራዎች፣ የኮዲንግ ስልጠና፣ በተለያዩ ኢኒሼቲቮች ትግበራ፣ በንቅናቄ የሚከናወኑ ተግባራት እና የገቢ አሰባሰብ ስራዎችን የማጠናከር ቀጣይ አቅጣጫዎች አስቀምጧል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በዝርዝር የተወያየው በቀረቡ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች እና አዋጆች ላይ ሲሆን፡-
የሶዶ ግብርና ኮሌጅ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ የከተሞች አደረጃጀት ፈርጅ ለውጥ የውሳኔ ሃሳብ እና አዋጅ፤ የURAP ደንብ፤ የጥቃቅን አነስተኛ እና መካከኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ድጋፍ ደንብ፤ በከተሞች ማስፋፊያ አከባቢ የሚታይ ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ጉዳይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሁም የታራሚዎች መኖን በተመለከቱ ረቂቅ ህጎች የውሳኔ ሀሳቦች ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረቡ ረቂቅ ደንቦችና አዋጆች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው ያፀደቀ ሲሆን፤ የቀረቡ አዋጆችን መርምሮ ለምክር ቤት መርቷል።
በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።