የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ ከአማካሪዎቻቸው ጋር የሥራ ስምሪትን በተመለከተ ውይይት አካሄዱ

(ዎላይታ ሶዶ ፦ መስከረም 22/2016 ዓ/ም) ትልቅ እድል አግኝቶናል፡፡ ይህ ታላቅ ህዝብ አደራም ጥሎብናል ፡፡ በመሆኑም በሚፈለገው መጠን ከሰራን ዕድሉ የታሪክ ተወዳሽ የሚያደርገን ሲሆን በተቃራኒው በአግባቡ ካልተጠቀምን የታሪክ ተወቃሽ መሆናችን የማይቀር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ነገር ግን ምቾታችንን ጥለን፤ ያለንን መልካም አጋጣሚ ሁሉ ወደ ተሻለ ውጤት ቀይረን የታሪክ ተወዳሽ ለመሆን ከመስራት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለንበት ክልል የእኛን ምቾትና ፍላጎት የምናስቀድምበት ሳይሆን የተሰበረውን ጠግነን፡ የተቀደደውን ሰፍተን፤ የተጨማደደውን አስተካክለን በመጠቀም የተሰጠንን ኃለፊነት ለመወጣት መዘጋጀትን በእጅጉ ይጠይቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሥነልቦናችንን ቅኝት በዚህ መልኩ በማስተካከል ከዚህ ቀደም የነበረንን መልካም ልምምድ እያጎለበትን መጥፎውን እያስወገድን በጊዜ የለኝም መንፈሰ፤ በአዲስ ወኔ እና አስተሳሰብ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መረባረብ ይኖርብናል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ባላችሁ ልምድና መልካም የስራ አፈጻጸም አሁን ያለውን ቦታ ይዛችኋል ያለው ክቡር አቶ ጥላሁን ከዚህ በኃላ የሚኖረን ቆይታ በስራና ባስመዘገብነው አፈጻጸም ይወሰናል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

አያይዘውም በአዲሱ ክልል ለአፈጻጸም ውደቀታችን ሰበባ ሰበብ መደርደርና ምክንያት ፍለጋ መኳተንን ክልሉ መሸከም የማይችል መሆኑን የገለጽት ርዕሰ መስተዳድሩ መሰዋዕትነት ከፍለን የክልሉን ልማት ለማረጋገጥ መነሳት ይገባል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ለአማካሪዎቸ የስራ ክፍፍል የተደረገ ሲሆን በተለያዩ ደንቦች ላይም ምክክር ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድርኩ የርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪና የአማካሪዎች ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ብርሃኑ ጌቦን ጨምሮ ሁሉም አማካሪዎች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply