ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ሰፋ ያለ ቆይታ የክልሉ መንግስት በመሬት ናዳና በጎርፍ አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ 19ሺ 847 ዜጎችን የመደገፍ እና መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በዚህ ክረምት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ የመሬት ናዳዎች እና የጎርፍ አደጋዎች በርካታ ዜጎችን ለሞት እና ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከወትሮው መጠኑ ከፍ ያለ የክረምት ወቅት ዝናብ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ አደጋዎች እጅግ ልብ ሰባሪ መሆናቸውን አስታውሰው፡-
በጎፋ፣ በወላይታ፤ በጋሞ እንዲሁም በባስኬቶ ዞኖች መጠናቸው የተለያየ ከፍተኛ ጉዳት በሰውና በንብረት ላይ ማድረሳቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጎርፍ ምክንያትም በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ላይ መፈናቀል ማጋጠሙንም ገልፀዋል።
እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ ለናዳ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የወላይታ፣ ጎፋ፣ ጋሞ፣ ባስኬቶ፣ አሪ እና ጋርዱላ ዞኖችን በማጥናት ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲወጡ መደረጉንና በቋሚነት ተጠንቶ በሰፈራ መልክ ለማቋቋም ሥራ መጀመሩንም አብራርተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በክልሉ 19 ሺህ 847 ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ እና መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የተፈናቀሉትን ሁሉ በቋሚነት ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር አስቸጋሪ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሰው ልጅ ቢኖርባቸው አስጊ የሆኑትንና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ቢሠራባቸው መኖር የሚያስችሉ ቦታዎችን የመለየት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰዎች በቀጣይነት ቢኖሩባቸው አደገኛ የሆኑ ቦታዎች የነበሩ ዜጎችን ወደ ሌሎች ስጋት ወደ ሌለባቸው ስፍራዎች በስግሰጋ እና በሰፈራ በቋሚነት በተለያዩ ዙሮች እንዲሰፍሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በመጀመሪያ ዙር 627 አባወራዎች እንዲሰፍሩ የሚደረግ ሲሆን በሁለተኛ ዙር ደግሞ 2ሺህ 394 አባወራዎች ሰፈራ እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል። ሰፈራውን ለማከናወንም ክልሉ ዝግጅቶችበማድረግ ላይ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።
ሌሎች በጥናት የሚለዩ መሆናቸውን አክለው ገልጸው፤ ለመኖር በሚያስችሉ ቦታዎች ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች አጠናክሮ በመስራት ወደ ቦታቸው የሚመለሱ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ አመላክተዋል።