
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት፤ 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ ያካሄደ ሲሆን፤ በጉባዔው የክልሉን መንግስት የስደስት ወር ሪፖርት እና የምክር ቤቱን የ3ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤ መርምሮ ከማፅደቁም ባሻገር፤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በጉባኤው የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ በዋና ዋና ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች፡- በግብርና፤ ትምህርትና ጤና፤ ኢንቨስትመንት፤ መሰረተ ልማት፤ ስራ ዕድል ፈጠራ፤ ገቢ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ እና መልካም አስተዳደር ዘርፍ በግማሽ የበጀት አመቱ በተሰሩ ስራዎች እና የተገኙ ውጤቶች ላይ በማተኮር ዝርዝር ሪፖርት አቅሪበዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቡትን የግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ተንተርሶ የምክር ቤት አባላት ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ በውይይቱ በክልሉ ባለፉ ስድስት ወራት የሚበረታታ ተግባራት መፈፀማቸውን በመግለፅ ለክልሉ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችንም አንስተዋል፡- በተለይ የመንገድ፣ መብራት፣ የውሃና የጤና መሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ፣ ሰላምና ፀጥታ፤ የስራ ዕድል ፈጠራን የተመለከቱ፤ የደምወዝ መዘግየት እንዲሁም ከግብርና ልማትና ከተለያዩ ኢንሼቲቮች ትግበራና ከትምህርት ጥራት ጋር የተያያዙና ሌሎች ጥያቄዎችን አቅርበዋል።



በምክር ቤት አባላቱ ለቀረቡ ጥያቄዎች ርዕሰ መስተዳድሩ እና ሌሎች የአስፈጻሚ ተቋማት ኃላፊዎች ሰፋ ያለ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ በመጨረሻም የክልሉን መንግስት የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡
ምክር ቤቱ የካቲት 7 እና 8/2017 ዓ.ም ለተከታታይ ሁለት ቀናት ባካሄደው በዚሁ 4ኛ ጉባዔው፡- በኢንቨስትመንት፣ በግብርና ኮሌጅ ማቋቋሚያ፣ በከተሞች ደረጃ ማሻሻያ እና በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ያተኮሩ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ በጉባኤው በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የቀርቡ የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ሹመቶችን ተቀብሎ በማፅደቅ፤ ለሁለት ቀናት ያካሄደው 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን በስኬት አጠናቋል፡፡