(ወላይታ ሶዶ መጋቢት 05/2016 ዓ.ም) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአርባ ምንጭ ከተማ ያካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው የክልሉ ርዕሰ መስትዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2016 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ርፖርት አቅርበዋል፡፡ ርዕሰ መስትዳድሩ በርፖርታቸው እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉ መንግስት በሁሉም አውታሮች በህግ አውጪ፣ በህግ አስፈፃሚ እና በህገ ተርጓሚ አመርቂ ስራዎችን በመስራት የክልሉን የሽግግር ጊዜ በስኬት አጠናቆ ወደ መደበኛ የልማትና ብልጽግና ስራዎች በፍጥነት በመሸጋገር ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻል እና የብልጽግና ለማድረግ በተሰሩ ሰፊ ስራዎች አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በክልሉ ህዝቦች የጋራ የመልማት ፍላጎት ላይ ማነቆ ሆኖ የቆየን ስር የሰደደ የነጠላ ትርክት እሳቤን ቀይሮ ገዥ የወል ትርክቶችን በማጽናት ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻል እና የብዝኅነት ተምሳሌት በማድረጉ ረገድ ውጤት ማምጣት መቻሉን ጠቅሰዋል።
ርዕሰ መስትዳድሩ በርፖርታቸው በዋና ዋና ዘርፎች በተለይም በግብርና፤ ጤና፤ ኢንቨስትመንት፤ መሰረተ ልማት፤ ስራ ዕድል ፈጠራ ፤ ገቢና የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት ዙራያ ባለፉት ስድስት ወራት በተሰሩ ስራዎች እና የተገኙ ውጤቶች ላይ በማተኮር ዝርዝር ርፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ በግብርና ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን ጉልህ ሚና መወጣት እንዲችል ከዕቅድ በላይ በተሰሩ የበልግ ወቅት ስራዎች ከ60 ሚሎየን ኩንታል በላይ ምርት የተገኘ ሲሆን፤ ከዓመታዊና ቋሚ ሰብሎች ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለነገ የማይባል የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ምርታማነትን ዘለቀታዊነት ባለው መንገድ ለማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻል፤ የግብአት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ማረም እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ፣ የተፋሰስ ልማት እና የሌማት ትሩፋት ስራዎችን በማጠናከር ለዘርፉ ውጤታማነት በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ በተለይ በጤና ተቋማት ግንባታና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሁም በቤተሰብ ዕቅድ እና ህብረተሰብ ጤና በርካታ ስራዎች ተሰርተው አበረታች ውጤት መመዝገቡ በርፖርቱ ተዳሷል። በኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ አስፈላጊ መስፈርት ያሟሉ ከ2.3 ብሊዬን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 55 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። ፕሮጀክቶቹ ከ10,000 በላይ ለሆኑ ዘጎች የስራ ዕድል ይፈጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪ በግማሽ የበጀት አመቱ በማዕድን ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በማቋቋሙ ረገድ ውጤታማ ስራ ከመሰራቱም በላይ ለ117,473 ዜጎች ስራ ዕድል በመፍጠር በርካታ ዜጎችን ወደ ስራ ማሰማራት መቻሉ በርፖርቱ ተመልክቷል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን በርዕሰ መስተዳድሩ ሰፊ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰቷቸዋል፡፡ በበጀት አመቱ ቀጣይ ቀሪ ጊዜያት በተለይ በገቢ አሰባሰብና የክልሉን ኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንገድና መሰረተ ልማት፣ በንፁሁ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በማህበራዊ ዘርፎች እንዲሁም በካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ትኩረት የሚደረግ መሆኑ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ጨምሮ ለምክር ቤቱ የቀረቡ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ በማጽደቅ፣ የክልሉን የህገ-መንግስት ጉዳዬች አጣሪ ኮሚቴ አባላት በመሰየም፣ በወንጀል የተከሰሱ የሁለት የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት በማንሳት እና በተጓደሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ምትክ ተተኪ አባል በመምረጥ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በስኬት አጠናቋል።