የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት የክልሉን የ 2017 በጀት ማከፋፈያ ረቂቅ ቀመር መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት 1ኛ ዙር 1ኛ ጉባኤዉን በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው 1ኛ ዓመት 1ኛ ዙር 1ኛ ጉባኤው የክልሉን በጀት ማከፋፈያ ቀመርን ጨምሮ የምክር ቤቱን የአሠራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብ፣ የ 2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ 2017 ዕቅድ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የበጀትና ቀመር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገረመው አያኖ ረቂቅ ቀመሩ 12ቱንም ዞኖች በሚጠቅም መልኩ ተከታታይ ዉይይቶችን በማድረግ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ከሁሉም ዞኖች አስፈላጊው አመልካች መረጃ ተሰብስቦና በቂ ግልፀኝነት ተፈጥሮ ወደ ቀመር ዝግጅት መገባቱን የጠቀሱት ሰብሳቢዉ ግልፀኝነትና አሳታፊነት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሠራር እንዲሁም ክልላዊ አንድነትን የማጠናከርና ሌሎች  መርሆዎችን ታሳቢ ማድረጉንም ገልፀዋል።   

ምክር ቤቱ የቀረበለት የ 2017 ረቂቅ የበጀት ማከፋፈያ ቀመር ዉሳኔ ላይ ሰፊ ዉይይት ካደረገ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ15 ቋሚ ኮሚቴዎችና ስብሳቢዎቻቸውን የዉሳኔ ሀሳብ መርምሮ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን የክልሉ የህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አባላት በመመረጥ በሙሉ ድምፅ ሰይሟል።

ምክር ቤቱ በክልሉ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖርና የማንነትና የፍትሃዊነት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኙ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ አዳማ ቲንጳዬ ገልፀዋል።

ዋና አፈ-ጉባኤው በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦች ቋንቋ እንዲያድግና እንዲጎለብት ምክር ቤቱ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረው ፀጥታ የሁሉም ሕዝቦች ቀዳሚ አጀንዳ በመሆኑ ክልሉን የሰላምና የብልፅግና ተምሳሌት በማድረግ ሂደት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

Leave a Reply