የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተረጂነት እሳቤ የተላቀቀ ማህበረሰብ በመገንባት እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናንና ብልፅግናን በማረጋገጥ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለመጎናፀፍ ለተያዘው ሀገራዊ ግብ ስኬት ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የክልሉ መንግስት ለግብርናው ልማት ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት፤ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ140 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት በማምረት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡
ክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን፤ የግብርና ልማት ዘርፉን ለማዘመንና ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ተረጂነትን ታሪክ የማድረግ ግብ ጥሎ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
በክልሉ መኸርን ጨምሮ በበልግና በመስኖ ልማት በአመት ሦሥቴ በማምረት፤ በምርት ዘመኑ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄ/ር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን፤ ከ156 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ በመሰራት ላይ ነው።
በተያዘው የመኸር እርሻ ብቻ ከ769 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት በዓመታዊና ቋሚ ሰብሎች በማልማት፤ ከ60 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ምርት ለመሰብሰብ የታቅደ ሲሆን፤ ለዚህም የተቀናጀ ርብርብ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
ክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ህዝቡን ከተረጂነት ለማላቀቅ በሚያደርገው ጉዞ፡-
በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ለይቶ የመጠቀም፤ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማላመድ፤ የአርሶ አደሩን የግብዓት አጠቃቀም የማሻሻልና የኩታ ገጠም እርሻን የማስፋት ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው፡፡
በዚህም በመኽር እርሻው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመልማት ላይ ያለው ሰብል፤ ክልሉ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማድረግ ላይ ያለው ሽግግር ውጤታማነት ከወዲሁ በሚያመላክት ቁመና ላይ ይገኛል፡፡
የመኸር እርሻው ተስፋ የሚሰጥና የግብርና ሽግግር ጉዞን የሚያሳልጥ ከመሆኑም ባሻገር፤ ምርታማነትን በማሳደጉ ረገድ በመመዝገብ ላይ ያለው ስኬት፤ አርሶ አደሩን ለላቀ ውጤታማነት ይበልጥ የሚያነሳሳም ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር፤ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና የክልሉን የብልፅግና ራይይ ዕውን በማድረግ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ፤ ክልሉ የግል ባለሀብቱን በግብርና ልማት በንቃት በማሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም የግል ባለሀብቱ በተለያዩ የግብርና ኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርቶ አልምቶ በመጠቀም ለክልሉ ዕድገት የድርሻውን እንዲያበረክት በማበረታታት አመርቂ ውጤት በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ዞኖች በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች፤ በአትክልትና ፍራፍሬ፤ በተቀናጀ ግብርና፤ በሰብልና በእንስሳት ሀብት ልማት፤ ቡና እና ሌሎች መስኮች እጅግ ውጤታማ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በማልማት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ የክልሉን ግብርና በማዘመኑ ረገድ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይም ናቸው፡፡
የክልሉ መንግስት በቀጣይ የግል ባለሀብቱ ከግብርና ምርት በተጨማሪ፤ በአግሮ-ፕሮሰሲንግና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሰማራት፤ እሴቶችን ጨምሮ የውጪ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ዕድገት የላቀ አስትዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል የሚሰራ ይሆናል፡፡
የግል ባለሀብቱ መዋዕለ ነዋዩን በክልሉ በማፈሰስ በተለይ በግብርና ልማት፤ በአግሮ-ፕሮሰሲንግና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርቶ፤ አልምቶ በመጠቀም የክልሉን ዕድገት እንዲደግፍ በዚህ አጋጣሚ ክልሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡