የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የካዎ ኮይሻ ወረዳ የመሬት ናዳ አደጋ ተጎጂዎችን ለመደገፍ ከወላይታ ዞን ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ይገኛል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን በካዎ ኮይሻ ወረዳ የተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ ለአደጋው ተጎጂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከወላይታ ዞን አስተዳደር ጋር በቅርበት በመስራት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ የአደጋው ተጎጂዎችን ከአካባቢው የማሸሽ እና በጊዜያዊ መጠለያ እንዲጠለሉ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡

በአደጋው 58 አባወራዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች እንዲጠለሉ በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡  

ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ የቁሳቁስ የሰብዓዊ ድጋፎችን ጨምሮ ጊዜያዊ መጠለያ ድንካኖች ወደ አካባቢው መላኩም ታውቋል፡፡ 

የክልሉ መንግስት ለአደጋው ተጎጂዎች ተጨማሪ አስፈላጊ ድጋፎችን ጨምሮ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከዞኑ አስተዳደር፤ ከፌዴራል አደጋ ስፋት ስራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት የሚሰራም ይሆናል፡፡

ተጎጂዎችን የመደገፍና በዘላቂነት የማቋቋም ስራውን በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ለመምራት የድጋፍ አሰባሳቢ፤ መልሶ ማቋቋምና የድጋፍ ስርጭት ዐቢይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ተግባራዊ ስራም ገብቷል፡፡

ለተጎጂ ወገኖች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፤ ባለሀብቶች፤ የግል ሰክተሩ እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጎጂዎችን በቋሚነት ለማቋቋም ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ተላልፏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የወላይታ ዞን የአደጋ ስጋት መከላከል ምክር ቤት ድጋፍ ለማሰባሰብ እንዲረዳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ፈንድ አካውንት ከፍቷል፡- 

     *CBE:- 1000643826217

በክልሉ ከወቅቱ የክረምት ዝናብ ጋር ተያይዞ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ በሁሉም አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ይመከራል።

Leave a Reply