የጂንካ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሸን ፕሮጀክት ግንባታ በተያዘው ጊዜ ተጠናቆ አገልገሎት እንዲሰጥ ለማስቻል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ወደ አሪ ዞን ጂንካ ከተማ ተጉዘው የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለጉብኝቱ ጂንካ ከተማ ሲደርሱ በክልል፣ በዞንና በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በአካባቢው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአሪ ዞን ቆይታቸው፥ የጂንካ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታ ያለበትን ደረጃ በመጎብኘት ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ የከተማው የውሃ ሪዘርቫየር ግንባታን የተመለከቱ ሲሆን፥ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ግንባታ 81 በመቶ መድረሱን ተመልክተዋል።

የጂንካ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ573 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመገንባት ላይ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ አገልገሎት የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

የፌዴራል ውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ስራውን ክትትል በማድረግ እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረው፥ የፕሮጀክቱ ግንባታ ውሃውን ከመደበኛ ፍሰት አጣርቶ ፖምፕ ማድረግ የሚቀር መሆኑን ገልፀዋል።

የጉብኝቱ ዓለማ ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ በመገምገም በተያዘው ጊዜ ተጠናቆ አገልገሎት መስጠት እንዲችል ከክልሉ መንግስት እና ከዞኑ አስተዳደር የሚጠበቀውን ለይቶ ድጋፍ ለማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጉብኝቱን ተከትሎ ርዕሰ መስተዳድሩ በፕሮጀክቱ ቀሪ ሥራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመከሩ ሲሆን፤  በምክክሩ የፕሮጀክቱ ግንባታ ቀሪ ሥራዎች የተመለከተ ሰነድ በአማካሪ ድርጅቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የጂንካ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በክልሉ ካሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በግንባታ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችንና ያሉ ማነቆዎችን ተነጋግሮ በአስቸኳይ በመፍታት ግንባታው ባጭር ጊዜ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡    

ፕሮጀክቱ በተለይ ከፋይናንስ አቅርቦት ችግርና ከአካባቢው ስነምህዳር ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ የግንባታ መጓተት አጋጥሞት ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አሁን ላይ የግንባታ ሥራው አስፈላጊ ጥሬ ዕቃዎች ቀርበው በመከናወን ላይ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ፕሮጀክቱ በዚህ ዓመት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ እና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት አጠናቆ የመጠጥ ውሃ አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም በአጽንኦት ገልፀው፤ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አስተማማኝና ዘላቂ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ካችመንቱ ላይ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ለዚህ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

አክለው የአካባቢው ህብረተሰብ ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ፤ የአካባቢ ጥበቃ ስራን በማጠናከር በግንባታው ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋና ጉዳት ቀድሞ መከላከል ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ግንባታውን በማከናወን አሁን ለደረሰበት ደረጃ ማድረስ ለቻለው የፕሮጀክቱ ተቋራጭ፡- ወገሬት ኮንስትራክሽን እና ለአማካሪ ድርጅቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረክ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው፤ በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታት ውሃውን ለህብረተሰቡ ባጭር ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክልሉ አዳኝ በበኩላቸው፤ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በክልሉ የቅርብ ክትትል ግንባታው በተሻለ ጥራት በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ግንባታውን እስከ ሰኔ 30 ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በመሰራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጂንካ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ120 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

Leave a Reply