የጠብ፣ የጥላቻና የውጊያ ትጥቅ በመፍታት ፍቅርና ሰላምን በመታጠቅ ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና መስራት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት በአርባ ምንጭ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርአት ተከብሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ማንሰራራት እንዲህ አይነት ታላላቅ በዓላትን ማክበር ሚናቸው የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አንድ ትልቅ ቤተ መፅሃፍት በመሆኗ ኢትዮጵያን ለማወቅ ብሔር ብሔረሰቦችን ማጥናት፣ ማወቅና መማር ያስፈልጋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ እምቅ ፀጋና ጥበብ ያላት ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያን በቅጡ በማወቅ ከግል ይልቅ በኢትዮጵያዊነት መሻት በጋራ እንቁም በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።
በመደመር እሳቤ በኅብረ ብሔራዊነትና በጋራ ትርክት ልባችንን ወደ ሠላምና ፍቅር በመመለስ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ መስራት ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከጦርነት ሰላም ይሻላል ብለው በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ መርጠው መጥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎችም ይህንን ፈለግ ተከትለው እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አባይ ተደምረን በህብረ-ብሄራዊ አንድነት ሰላምን በማስቀደም የማያልፍ ታሪክና አሻራችንን እናሳርፍ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጠብ፣ የጥላቻና የውጊያ ትጥቅ በመፍታት ፍቅርና ሰላምን እንታጠቅ ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው በመደመርና በስራ ትጋት በመሆኑ ሰላምን በማስቀደም በህብረ-ብሄራዊነት በጋራ እንቁም በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።