“ያሉንን ፀጋዎች ተጠቅሞ በማልማት ወደ ባለፀግነት ለመሸጋገር ተግቶ መስራት ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር የግብርና ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው፤ በወላይታ ዞን፤ በሁምቦ ወረዳ ሾጮራ ኦጎዳማ ቀበሌ ተገኝተው፤ በ157 ሄ/ር መሬት ላይ በተያዘው የመኽር እርሻ በክላስተር በመልማት ላይ ያለ የጤፍ ሰብል ተመልክተዋል።

በቀበሌው በክላስተር በመልማት ላይ የሚገኘው እርሻ፤ 242 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ ከ 2 ሺህ 3 መቶ ኩ/ል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አቅደው በማልማት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።    

በተመሳሳይ ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዞኑ ሁምቦ ወረዳ፤ ኮይሻ ጎላ ቀበሌ በወጣቶች በክላስተር በመልማት ላይ የሚገኝ የጤፍ ሰብል ጎብኝተዋል።    

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ፤ ወጣቶች በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ በማህበር ተደራጅተው በ175 ሄ/ር መሬት ላይ በክላስተር በማልማት ላይ የሚገኙትን የጤፍ ሰብል የተመለከቱ ሲሆን፤ ያሉንን ፀጋዎች ተጠቅሞ በማልማት ወደ ባለፀግነት ለመሸጋገር ተግቶ መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡   

አክለው፤ በግብርና ልማት ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናችንን ከማረጋገጥ ባለፈ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በማሳለጥ ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን ለማረጋገጥ ያሉንን ሀብቶች አሟጠን ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።    

በቀበሌው በወጣቶች እየለማ የሚገኘው የጤፍ ክላስተር፤ ክልላችን በግብርናው ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ያሳየን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ተግተንና ተባብረን በመስራት ከተረጂነት ተላቀን ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር መታተር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ ሰብልን በክላስተር ማልማት ተገቢውን ድጋፍ በማግኘት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር፤ የአርሶ አደሩን ጉልበት በመቆጠብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

በምርት አሰባሰብ ወቅት የሚከሰት ብክነትን ለመቀነስ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የወጣት ማህበራቱ ተምረን ስራ አጥ ሆነናል ለሚሉ ወጣቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል።

Leave a Reply