ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን ጎበኙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፤ በአርባ ምንጭ ቆይታቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን የሚገኘውን የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ በፓርኩ ክልል ያለውን 40 ምንጮች የሚገኙበትንና በተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች የሚታወቀውን የአርባ ምንጭ ደን/ጫካ ተመልክተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የሳቫና የሳር ምድርን፣ የደን እና የውቦቹን የአባያ እና ጫሞ ሃይቆች ብሎም የሌሎች ሳቢ መዳረሻዎች መገኛ ያሉት አካባቢ ሲሆን፤ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውብ ኅብር የታወቀ የተፈጥሮ መስህብም ነው።    

514 ስኩዌር ኪሎ ሜትሮች የሚሰፋው ፓርኩ፤ አይነተ ብዙ ለሆኑ እንደ የሜዳ አህያ፣ አጋዘን፣ አዞ ዓይነት የዱር እንስሳት ብሎም ከ270 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መገኛ በመሆኑ ለተፈጥሮ ጉብኝት አፍቃሪዎች የልብ የሚያደርስ አይነተኛ ስፍራ ነው።

በሀገራችን እንደሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች ነጭ ሳር የተፈጥሮ ሥነምኅዳርን በመጠበቅ እና ቱሪዝምን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑ ይታወቃል፡፡     

በጉብኝቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፤ ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፤ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply