ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ፤ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት እና ሌሎች የግብርና የልማት ስራዎችን ጎበኙ      

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አርባምንጭ ከተማ ገብተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለክብረ በዓሉ አርባምንጭ አለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ደማቅ የሆነ አቀባበል የተደርገላቸው ሲሆን፤ መላው የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎችም በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለክብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደማቅ የሆነ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ቆይታቸው፤ ከ19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ጎን ለጎን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡        

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በዚሁ ጉብኝታቸው በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው የተለያዩ የልማት ስራዎችን የተመለከቱ ሲሆን፤ በተለይም የፍራፍሬ ችግኞች ማፍያ ፕሮጀክት፣ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተሰሩ ስራዎች ማሳያ፣ የገበታ ለትውልድ ፕሮጄክት ያለበት የግንባታ ሂደት እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ በመከናወን ላይ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ስራን ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ “አርባ ምንጭ ላይ ያየነው የክላስተር ኢንሸቲቪ ተስፋ ሰጪ ነው” ያሉ ሲሆን፤ በተለይ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አስመልክቶ የሚከተለውን መልዕክት አጋርተዋል፡-    

ከአምስት ወራት በፊት ከነበረኝ ጉብኝት በመቀጠል ዛሬ የአርባ ምንጭ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ገምግመናል። ይኽ ሥራ የሀገራችንን የቱሪዝም አቅም የሚያጠናክር የአካባቢውን አስደናቂ የተፈጥሮ መልክዓ ምድር እና የተትረፈረፈ ሀብት ቆጥሮ የሚጠቀም ሁሉን ያካተተ ነው። ቱሪዝምን ከማሳደግ ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ፕሮጀክቱ ትርጉም ባለው ደራጃ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። እነዚህን መሰል ሥራዎች በስኬት ሥራ ሲጀምሩ ለዘላቂ ልማት እና ብልፅግና መንገድ የሚጠርጉ ይሆናሉ“።  

በአጠቃላይ በአርባምንጭ ከተማ የተካሄደው ጉብኝት፤ የኢኮኖሚ እድገትን በከተማም ሆነ በክልል ደረጃ በመምራት ምሰሶ በሆኑት በግብርና ምርታማነት፣ በከተማ መሠረተ ልማት እና ቱሪዝም ልማት ዘርፍ በክልሉ አርባ ምንጭ እያሳያችው ያለው እድገት የታየበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በጉብኝቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፤ ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፤ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply