ጥላቻን በፍቅር፤ ጥርጣሬን በእምነት በመቀየር የህዝብ ለህዝብ ትስስራችንን ይበልጥ አጠናክረን ለክልላችን ዕድገት እና ለህዝባችን ሁለንተናዊ የጋራ ተጠቃሚነት ሊንረባረብ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ አመት ታሪካዊ የምስረታ ክብረ በዓል “ከነሐሴ እስከ ነሐሴ” በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡    

የክብረ በዓሉ አካል የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “ከነሐሴ እስከ ነሐሴ” በሚል ርዕስ የክልሉን ምስረታ ሂደት እና የተከናወኑ ዐቢይት ተግባራት የዳሰሰ መነሻ ፅሁፍ ለተሰብሳቢው አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በፁሁፋቸው የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመገንባት ዉጥን በመያዝ በተጀመረዉ ጉዞ በቅድመ-ምስረታ፣ በምስረታ እና በድህረ-ምስረታ ወቅት የተከናወኑ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን፤ ለተሰብሳቢው ገለፃም አድርገዋል።  

በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ትኩረትን ሙሉ በሙሉ በልማት ላይ በማድረግ ለስኬት ለመብቃት፤ የክልሉን የአንድ ዓመት ጉዞ በመፈተሽ በማህበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተከናወኑ ዐቢይት ተግባራትን መዳሰስ ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በጹሁፋቸው አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሽግግር ጊዜና መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ በመግባት፤ ክልሉን ከማደራጀት ጀምሮ በሁሉም አውታሮች በተሰሩ ስራዎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡  

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የምስረታ ሂደት ያጋጠሙ የተለያዩ ተግዳሮቶች ለህዝቦች የዘመናት አብሮነት፤ ዘላቂ ሰላም፤ ልማት እና የጋራ ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠት ክልሉን በስኬት ማደራጀት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ሲነሱ ለነበሩ ያደሩ የአደራጃጀትና የመዋቅር ጥያቄዎችም በሕገ-መንግስታዊ ማዕቀፍ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ቃልን በተግባር ማረጋገጥ ማቻሉን ተናግረዋል፡፡     

በሽግግር ምዕራፍ ክልሉን በስድስት ማዕከላት አደራጅቶ ተቋማዊ አሰራር በመዘርጋትና በየማዕከላቱ ደማቅ የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሮች በማካሄድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ብቃት ያለው ያልተማከለ አገልግሎት መስጠት ተችሏል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው፤ አስፈላጊው የህግና የአሠራር ስርዓቶች መዘርጋታቸውንና በዚህም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያግዙ 52 አዋጆች፣ 85 ደንቦች እና ከ 74 በላይ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

የክልሉን ምስረታ ተከትሎ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በተሰሩ ስራዎች ክልሉን አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት፤ የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ክልል ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎችንና የሰላም ግንባታ ተግባራት በማጠናከር የክልሉን ሰላም ማፅናት እንደ ሚገባም ተናግረዋል፡፡   

ከዚህ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ስጋት የሆኑ ቀጠናዎችን አስቀድሞ በመለየት እና ከኅብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን አስቀድሞ መግታት ይገባል ብለዋል።

ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ከምንም ጊዜ በላይ ሰላማችንን ለማስጠበቅ መስራት ይገባናል ያሉት ርዕለ መስተዳድሩ፤ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ክልሉን የሰላም ተምሳሌት በማድረጉ ረገድ የተለመደ ጉልህ አስትዋጽኦቸውን በማጠናከር መስራት ይገባቸዋል ሲሉም ገልፀዋል።

በክልሉ የአንድ አመት ጉዞ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር በመስራት አላስፈላጊ ጥርጣሬዎችን በዉይይትና በመተማመን ለማስወገድ መሰራቱንም በቀረበዉ ፅሁፍ አንስተዋል።

የክልሉን ፀጋዎች በመለየት አልምቶ ለመጠቀም ለግል ባለሀብቱ የማሳወቅ ስራ በመስራት በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቅሰው፤ በኢንቨስትመንት በኩል ከዚህ ቀደም የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት አልሚ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ሰው ተኮር ተግባራትን በተመለከተ በክረምት በጎ ፈቃድ በክልሉ በአንድ ጀንበር ከ4 ሺህ 5 መቶ በላይ ቤቶች መገንባት መቻሉንም ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት ለነገ ስንቅ ይሆነን ዘንድ ለመርዳት፤ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደገፍ ሁሌም ዝግጁ የሆነ፤ በበጎነትና በመረዳዳት የሚያምን ታታሪ ህዝብ አለን ያሉ ሲሆን፤ ህዝባችንን ተጠቅመን ክልላችንን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕያችን ስኬት ሊንሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡  

ከዚህም በተጨማሪ ክልሉ የተሻለ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት በመሆኑ፤ ያሉንን ፀጋዎች በመለየትና አሟጠን በመጠቀም ለክልላችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት መትጋት ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል።  

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው አመራሩም ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን የአመለካከትና የተግባር አንድነትንና የአላማ ፅናትን በማጠናክር ለህሊናው ተገዢ ሆኖ ህዝቡን በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።

የህዝብ ለህዝብ ትስስሮችን ይበልጥ በማጠናከር፤ የደግነትና የዕርቅ መንገዶችን በመጠቀም ጥላቻን በፍቅር፤ ጥርጣሬን በእምነት በመቀየር ለክልላችን ዕድገት እና ለህዝባችን ሁለንተናዊ የጋራ ተጠቃሚነት መረባረብ እንደሚገባም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የአንድ አመት ጎዞ የተለያዩ የልማት ኢንሼቲቮችን በመተግበር፤ በተለይ በግብርና ልማት፤ ቱሪዝም፤ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለማላቀቅ የሚያስችሉ ከወዲሁ መሰረት የጣሉ ውጤታማ ስራዎችን መስራት መቻሉም ተመላክቷል፡፡

የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ሽግግር በማፋጠን የህዝቡን ሁሉ አቀፍ ልማትና ብልፅግና ለማሳካት የሚያስችል የቀጣይ ሰባት (7) ዓመት የፍኖተ ብልፅግና መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉም በርዕሰ መስተዳድሩ ተገልጿል፡፡

የወጪ ፍላጎትና ገቢ አለመጣጠም፣ በከተማና በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ አለመሆን እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች በክልሉ የአንድ ዓመት ጉዞ ካጋጠሙ ውስንነቶችና ችግሮች የሚጠቀሱ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል፡፡

የህዝቡን አንድነት ይበልጥ ማጎልበትና የክልሉን ሰላም ማፅናት፤ ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ለይቶ በመጠቀም የህዝቡን የመሰረተ ልማትና ሌሎች የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

Leave a Reply