19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል እጅግ በደመቀና ባማረ ሁኔታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ተከብሮ በስኬት ተጠናቋል

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በውቢቷ አርባምንጭ ከተማ ጅግ በደመቀ እና ባማረ ሁኔታ በስኬት ተክብሯል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ክብረ በዓሉን የማዘጋጀት ኃላፊነት ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ፤ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አመራር እና የቅርብ ክትትል አስቀድሞ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን፤ ይህን ታላቅ ሀገራዊ ኩነት በብቃት ማዘጋጀት ችሏል፡፡

ክብረ በዓሉ በተለያዩ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ባጎለበቱ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገፅታን ባጎሉ እንዲሁም የክልሉን በርካታ ሀብቶች እና ልዩ ልዩ ፀጋዎች ለአለም ባስተዋወቁ መርሃ ግብሮች በስኬት ተከብሯል፡፡

በዓሉ ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ሲያሜዎች፡- የወንድማማችነት ቀን፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን፤ የብዝኅነት ቀን፤ የምክክር ቀን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀን በሚል በተለያዩ መርሃ ግብሮች የተከበረ ሲሆን፤ ለአብነት ለመጥቀስ ያህል፡- ታላቁ ሩጫ፤ የንግድ ትርኢትና ባዛር፤ የባህል ኢግዚብሽንና ፌስቲቫል፤ የጎዳና ላይ የባህል ትርዒቶች፤ ስምፖዝዬም፤ የአብሮነት ማዕድ (የእራት ፕሮግራም) እንዲሁም የክብረ በዓሉ ማሳረጊያ በስታዲዮም በድምቀት ተከብሯል፡፡ 

“ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 25 እስከ ህዳር 29 ከፍ ባለ ድምቀት የተከበረው በዓሉ፤ ኢትዮጵያዊን ከአራቱም ማዕዘናት ተሰባስበው፤ በአስደናቂ ብዝኅ ባህሎቻቸውና እሴቶቻቸው አጊጤው፤ በማንነት መገለጫ ቀለሞቻቸው አሸብርቀው ዘመን የተሻገረ አብሮነታቸውንና በኅብረ-ብሔራዊነት የተገነባ አንድነታቸውን አክብረዋል፡፡ 

በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁ ስብስቦች ሳይሆኑ፤ በዘመናት አብሮነት የተዛመዱ፤ የተጋመዱ እና ባህል እሴቶቻቸውን ተወራርሰው የተሠናሠሉ መሆናቸውን በተግባር ያሳዬም ሆኖ አልፏል፡፡

ኢትየጵያን የሚያሻግሩ የሰላም፣ የብዝኃነት፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የኅብረ-ብሔራዊነት እሴቶች፣ ቱባ ባህሎችና ሥርዓቶች መገኛ በሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተከበረው በዓሉ፤ ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ የኅብረ-ብሔራዊነት መሰረት ላይ ለማፅናት መሠረት የጣለም ነበር፡፡

ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚለዉ መሪ ቃል፤ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ እዉነታዎችን ቁልጭ አድርጎ ያሳዬም ሲሆን፤ ክብረ በዓሉ በአርባ ምንጭ ከተማ መሰናዳቱ፤ ክልላዊ ብዝሃነትን እና አካታችነትን ክልሉ ካለው እምቅ አቅምና ፀጋዎች ጋር ለማስተዋወቅ ዕድል የፈጠረም ነው።

ከዚህም ባለፈ በዓሉ የአንድነት፣ የሰላም፣ የመቻቻል እንዲሁም የሕብረ-ብሔራዊነት ቀለም መገለጫ ሆኖ ከመከበሩም በላይ፤ ኢትዮጵያውያን የብዝሃ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴትና የተፈጥሮ መስህብ ባለቤት መሆናቸውን ለዓለም ያስተዋወቁበት መድረክ ሆኖ አልፏል፡፡

በክብረ በዓሉ ማጠቃለያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫን ከባለፈው ዓመት የበዓሉ አስተናጋጅ ሶማሌ ክልል የተረከበ ሲሆን፤ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እንዲያዘጋጅ ተወስኗል።

በክብረ በዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፤ ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፤ የህዝብ ተወካዮች ፣ክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ ሌሎች የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፤ ሚኒስትሮች፤ ከንቲባዎች፤ አምባሳደሮች፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል አምባሳደሮች፤ የኃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግለዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply