19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችል በቂ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መልዕክት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በአርባ ምንጭ ከተማ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ አዘጋጅነት በአርባ ምንጭ ከተማ በሚከበረው 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክብረ በዓል አከባበር ዙሪያ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ዐቢይ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡   

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ፤ የክልሉ መንግስት በኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በክልሉ አዘጋጅነት በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት ለሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክብረ በዓል ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ ዘርፈ ብዙ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ፤ የህዝቦች ትስስርን በማጠናከር እና በማጎልበት ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ከፈ ያለ ፋይዳ አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውንና ማንነታቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ አዘጋጅነት የሚከበረው የዘንድሮ በዓል፤ በይዘትም ሆነ በድምቀት ለየት ባለ ሁኔታ ክልሉን በሚመጥን እና የክልሉን ገፅታ እንዲሁም የክልሉን የባህልና የቱሪዝም ፀጋዎች በሚያጎላና በሚያስተዋውቅ መልኩ ለማክበር በቂ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክሩና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጐለብቱ ኩነቶች በድምቀት ለማክበር መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

ክልሉ ለበዓሉ ዝግጅት አስቀድሞ ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወደ ዝግጅት መግባቱን ጠቅሰው፤ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በየጊዜው ስራዎችን በመገምገም ቀጣይ በሚኖረው አጭር ጊዜ ውስጥ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ስራውን በአፋጣኝ ለማጠናቀቅ የዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴ አባላት፤ ለስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት ቀሪ ስራዎችን ለይተው በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።  

ፌደረሽን ምክር ቤትም በዓሉ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የፌደሬሸን ምክር ቤት ዐቢይ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው፤ በዓሉ የሀገርን ብሎም የክልሉን ገፅታ የሚገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክልሉ ይህን በመገንዘብ በቂ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን በመግልጽ አድንቀዋል፡፡

ከውይይቱ በተጨማሪ፤ ርዕሰ መስተዳድሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ልዑካን ጋር  የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክብረ በዓል የሚከበሩባቸውን ስፍራዎች ዝግጅት በአርባ ምንጭ ከተማ ተዘዋውረው ጎበኝተዋል።

Leave a Reply