ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን በመሰረትን የመጀመሪያ ዓመት የማህበራዊ ብልፅግናችን ትልም ማሳኪያ የሆነው ሰው ተኮር ፕሮጀክታችንን ማስመረቅ በመቻሉ ፈጣሪን አመሰግናለሁ ብለዋል።
ክልላችን የተፈጥሮ ፀጋዎች መናገሻ፤ የብሔር ብሔረሰቦች መድመቅያ፤ የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት፤ የአብሮነትና የፍቅር ሙዳይ፤ የጥበብ መፍለቅያ፤ የትጉ እና የታታሪ ህዝቦች መኖሪያና የፈጣሪ ደግነት ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው የሰው ልጆች ያለ ልዩነት የሚኖሩባት የትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌት፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ስድስቱ የክልል ማዕከላት አንዷ ወደ ሆነችው ምድር ገነቷ አርባምንጭ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል።
አርባምንጭ ምንም እንኳን በተፈጥሮ ፀጋ የበለፀገች፤ በሰላም አምባሳደር አባቶች የተመሰረተች፤ ከሁሉም ለሁሉም የሆነች ብትሆንም የሚገባት ቦታ ፣ ክብር እና ተገቢው ልማት ተነፍጓት የቆየች ከተማ እንደሆነችም ገልፀዋል።
ይህን ታሪኳን ሽሮ መልኳንና ውበቷን በመግለጥ፤ ፀጋዋንና ማንነቷን በማስተዋወቅ ዛሬ ሁሉም ቀልቡን ሚጥልባት፤ የዓለም ዓይን የሚያርፍባት፤ የበለጠ የቱሪዝም መናገሻ፤ የለውጡ ትሩፋት ሁነኛ ማሳያ እንድትሆን ለመረጣት ክቡር ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመሰራረት የእዉነተኛ ዴሞክራሲ መገለጫ፣ ቃልን በተግባር ማሳያ የሆነና በስድስት የክልል ማዕከላት ተደራጅቶ ወደ ተግባር በመግባት ክልሉን የሠላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ድንቅ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ለዚህም በክልሉ የምስረታ ሂደት የመላዉ ህዝባችን ፍላጎትና ተሳትፎ እንዲጠበቅ በቅርበት የደገፉን፣ የሀገራችን ጊዜያዊ ፈተናዎችን ወደ ምቹ አጋጠሚዎችና ዕድል በመቀየር የታሪክ እጥፋት ያስመዘገቡ፣ የዓለም የሠላም ኖቢል ሽልማት ተሸላሚ፣ ለአየር ለዉጥ መዛባት ፍቱን መፍትሄ አፍላቂ፣ በሀገራችን ስር የሰደደዉን የተረጂነት አስተሳሰብ በመድፈቅ ከዘመናዊ ባሪነት ቀንበር ነፃ አዉጪ፤ መንፈሰ ጠንካራ፣ ያመኑትንና እና ያለሙትን በመተግበር ከአገር አልፎ ለአህጉራችንና ለአለማችን ፍቱን የሆነዉ የመደመር ዕሳቤ ባለቤት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በድጋሚ ምስጋናዬ ይድረሶት፣ ፈጣሪ ረጅም ዕድሜ እና ሙሉ ጤናን እንዲያድሎት ምኞቴም ነው ብለዋል።
የብልፅግና ቱሩፋት የሆነዉ ክልላችን ከተመሰረተ ዓመት ያልሞላዉ ቢሆንም ስድስቱን የክልል ማዕከላት ከማደራጀት አልፎ የመንግስትን ውጤታማ ስራን የሚደግፉ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት በሙላት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
ዜጎቻችን ያልተማከለ አገልግሎት በተሻለ መንገድ እንዲያገኙ በማድረግ የህግ አውጭ፤ ተርጓሚ እና አስፈፃሚ ተቋሞቻችን የህዝብን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉም ተደርጓል ብለዋል።
በአሁን ወቅት የበለፀገ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት የሆነዉ ክልላችንን የሰላም፤ የመቻቻል እና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ላስቀመጥነው ራዕይ ዕውን መሆን በመረባረብ ላይ እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የክልላችንን ህዝቦች ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሳካት የሚያስችል የመጪዉ ዘመን ፍኖተ ብልፅግና ዕቅድ በማዘጋጀት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለማላቀቅ እየተጋን፤ የገጠሙንን የተለያዩ ስብራቶች እያከምን የህዝብ ለህዝብ ትስስሮች እያጠናከርን በስኬት በመጓዝ ላይ እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።
በአጭር ጊዜም ከራስ አልፎ ለሌላው መትረፍ የሚችል፤ የተትረፈረፈ ምርት እና የገቢ አቅም ያለው ክልል እንደምናደረግ እምነቴ የፀና ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መሪያችን እንቅልፍ የማያውቅ፤ አሻግሮ ሩቅ የሚያይ፤ ሰርቶ የሚያሰራና ሌለውጥ የሚተጋና ሙሉ ጊዜውን ሰውቶ የሚደግፍ በመሆኑ የታለመውን ውጤት ከሚጠበቀው ባጠረ ጊዜ እንደምናስመዘግብ ልበ ሙሉ ነኝ ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለክልላችን ከፌደራል መንግስት በመጀመሪያ ምስረታ ዓመት የተለገሰ ልዩ ስጦታ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂ የተደራጀው ሆስፒታሉ ክልላችን ካለዉ የቱርዝም ፀጋ በተጨማሪ የህክምና ቱርዝም ማዕከል ባለቤት በማድረግ የማህበራዊ ብልፅግናችንን ማረጋገጫ የሚሆን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህ እጅግ ዘመናዊና በላቀ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ያለጥርጥር በክልላችን የጤና ሽፋን ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ይታመናል።
ከዚህም በላይ የልህቀት ማዕከል ሆኖ በማገልገል ፈጠራንና ምርምርን የሚያበረታታ እና በሕክምናው ዘርፍ የአዳዲስ ዕውቀቶች ግኝት መፍለቂያ ምንጭ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ዘመናዊ የጤና ተቋም ጤናማ እና አምራች ዜጋ በመፍጠር ለብልፅግና ራዕያችን ስኬት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ እሙን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሆስፒታሉ ዛሬ በዚህ መልኩ ግንባታው በስኬት ተጠናቆ ለምረቃ እንዲበቃ ከቅረብም ከሩቅም ድጋፍ ላደረጋችሁ በሙሉ በራሴና በመላ የክልሉ ህዝብ ስም የላቀ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡