መስተዳድር ምክር ቤቱ 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን በወላይታ ሶዶ ከተማ ያካሄደ ሲሆን፤ በስብሰባው የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም በመገምገም እና በ2017 ዕቅድ ዝግጅት ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በስብሰባው በዋናነት የበጀት አመቱን የክልሉ መንግሰት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎች፤ የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በጥልቀት ተወያይቷል፡፡
ምክር ቤቱ በተለይ በክልሉ በሰላምና ፀጥታ፤ በመልካም አስተዳደር፤ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የነበሩ አፈጻጸሞችን ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡
የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ የመሩት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በውይይቱ ገንቢ ሃሳቦች መነሳታቸውን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት በበጀት አመቱ መላው የክልሉን ህዝብ አስተባብሮ በሰራው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በህዝብ ይሁንታና ድጋፍ የተመሰረተ እንደመሆኑ በክልሉ የሰላም እና ልማት ስራዎች ህዝቡን በንቃት በማሳተፍ መስራታችን ለተሻለ ውጤት አብቅቶናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ከህዝባችን ጋር ተደጋግፈን በመስራት የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ክልሉ በርካታ ፀጋዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ በተለይ በግብርና ልማት ያለንን አቅም በመለየትና የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን በመቀጠል በተለይ በሆርቲካልቸር፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ክልሉ ባለው ፀጋ ልክ በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እምቅ አቅም ያለው መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለውጤት በማብቃት ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ በበጀት አመቱ ከሰላምና ፀጥታ አንጻር ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በተሰሩ ስራዎች በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን የተመለከተ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የክልሉ መገለጫ የሆነውን የሰላም ተምሳሌትነት አስጠብቆ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑም በስብሰባው በአጽንኦት ተገልጿል፡፡
በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በንቅናቄ በተሰሩ ስራዎች በተለይ በአንድ መፅሃፍ ለአንድ ተማሪ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፤ የከተሞች ፅዳትና ብክለት መከላከል፤ የተራራ ልማት እና ሌሎችም ስራዎችን በህዝብ ተሳትፎ በተቀናጀ አግባብ በንቅናቄ በመምራት መልካም ውጤትና ተሞክሮ መገኘት መቻሉም ተገምግሟል።
በበጀት አመቱ ያሉ የሀብት ውስንነቶችን በመቋቋም እንዲሁም ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን በመዘርጋት በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆን መቻሉም በስብሰባው ተመልክቷል፡፡
በተለይ በበጀት አመቱ መስተዳድር ምክር ቤቱ አብዛኛወን ስብሰባ በበይነ መረብ ማድረጉ እና ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ስራዎችን መስራት መቻሉ እንደ መልካም ተሞክሮ የሚጠቀስ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የከፍተኛ ፀጋ ባለቤት የሆነው ክልሉን እንዲንመራ የተሰጠንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በቀጣይ አመራሩ በጊዜ የለኝም መንፈስ በመስራት የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ መስራት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በቀጣይ የክልሉን የውስጥ አቅም ለማጎልበት ለገቢ አሰባሰብ ስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ በመሰበሰብ በራስ አቅም የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ መስራት እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም መስተዳድር ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት የ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ከነማሻሻያው በማጽደቅ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲመራ በሙሉ ድምፅ ወሳነ አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በቀጣይ የ2017 በጀት አመት ዕቅድ ዝግጅት ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በመለየት እና የ2017 በጀት አመት የበጀት ድልድል መነሻ ሀሳቦች ዙሪያ በመምከርና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡