ክልላዊ የሀብት አስተዳደር እና የገቢ አሰባሰብ ስራዎች ልዩ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሄደ

“ፀጋዎቻችንን አሟጠን በመሰብሰብ አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም እንፈጥራለን፣ የክልላችንን ብልፅግና እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ሃሳብ ክልላዊ የ2016 በጀት ዓመት የሀብት አስተዳደርና የገቢ አሰባሰብ ስራዎች ልዩ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መድረኩ የገቢ አሰባሰብ አቅማችን ያለበትን ደረጃ እንዲሁም እስከ አሁን የተሰበሰበውን ገቢ እና የወጣውን ወጪ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመመልከት በቀሪ ጊዜያት በቁጭት ወደ ተግባር ለመግባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ያለበትን ደረጃ ከፍ ለማድረግ የውስጥ አቅምን በማጎልበት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ክልሉ ባለው ፀጋና ሀብት ልክ ፍታሃዊ ገቢ መሰብሰብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

ጤናማና ፍታሀዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓትን መዘርጋትና ማዘመን የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄዎች እና አዳጊ የመልማት ፍላጎት በብቃት ለመመለስ የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ይፈጥራል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።   

ግብርን ከመሰብሰና ማስተዳደር ጋር ያሉ ክፍተቶችን በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባም የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በፋይናንስ ስርዓቱ ገቢ በሌለበት ወጪን ማብዛት ክልሉን ለአላስፈላጊ ብክነት መዳረግ በመሆኑ ከወዲሁ ሊታረም የሚገባው መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።  

ታክስን በተገቢው መንገድ የማይሰበስብ መንግስት ለህብረተሰቡ የመልማት ጥያቄ ምላሽ መስጠት አይችልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በማዘመን እና ያሉንን ፀጋዎች በመለየት ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባ አብራርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

በሁሉም አማራጮች የገቢ አሰባሰብን አሟጦ በመጠቀም የክልሉን ልማት ለማረጋገጥ የአመራሩ ቁርጠኝነት እና የጋራ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው የክልሉን የፋይናንስ ስርዓት የሚያዛቡ አሠራር ሊታረሙ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ በ2016 በጀት አመት በፋይናንስ ስርዓት ውስጥ የወጪ ቅነሳ መመሪያን ተከትሎ አለ መፈፀምና በየጊዜው የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መከሰት እንዲሁም ያልታቀዱ ግዥዎች በከፍተኛ ሁኔታ መኖራቸውንም አንስተዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው ባለፉት 10 ወራት የክልሉ የገቢ አቅምና በተጨባጭ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የህግ ማስከበር ስራዎች ደካማ መሆንና የዞኖች የገቢ አሰባሰብ ውጤታማነት ላይ ክፍተት መኖር በአፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ውስንነቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በግብር ከፋዮች ዘንድ የታክስ ስወራ፣ ደረሰኝ አለመቁረጥ በዋናነት የሚፈፀሙ የህግ ጥሰቶች መሆናቸውን ያብራሩት ኃላፊዋ በክልሉ 129 የስነ ምግባር ጥሰት የፈፀሙ የገቢ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት በቀጣይ ለፋይናንስ እና ለገቢ ስርዓቱ ውጤታማነት ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

Leave a Reply