በደቡብ ኢትዮጵያ እና በኦሮሚያ ክልሎች ቀጠናዊ የሠላምና ፀጥታ ዙሪያ በአርባምንጭ ከተማ ምክክር ተካሄደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና በመከላከያ ሚኒስትር የደቡብ እዝ አዛዥ ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ እና በኦሮምያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ቀጠናዊ ሠላምና ፀጥታ ዙሪያ የጋራ ምክክር በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የጀመርነውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ በስኬት ለማስቀጠል በቀጠናው አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ቀጠናው ሠላምና ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማስቻል ለአንድ አካል የሚተው ኃላፊነት አለመሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በቀጠናው አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የጋራ ዕቅድ አውጥቶ መስራትና መመራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የኦሮሚያና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች፣ የዞን እና ወረዳ  ከፍተኛ  አመራሮች፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ እና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።

በምክክሩ በቀጣይም ተከታታይነት ያለው ግንኙነትን በማጠናከር የቀጠናውን ሠላምና ፀጥታ በጋራ ተቀናጅቶ በመመራት አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

Leave a Reply