“የህዝብ ጥያቄን በብቃትና በጥራት መመለስ እና ጠንካራ መንግስትና ሀገር መፍጠር የሚቻለው ፍትሃዊና ተአማኒ ገቢን በአግባቡ ሰብስቦ ልማት ላይ ማዋል ሲቻል ነው”-  ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ 2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም፣ የ 2017 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የታክስ ህጎች ትዉዉቅ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።   

መድረኩ በክልሉ በጎፋ እና በወላይታ ዞኖች በደረሱ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ህይወታቸው ላጡ ወገኖች የህሊና ፀሎት በማድረግ ተጀምሯል።

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአንድ መንግስት ጥንካሬ መለያ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ የህዝብ ጥያቄን በብቃት መመለስ መቻል ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህን ለማሳካት የውስጥ አቅምንና ፀጋን በመለየት አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሀገራችን ባለፉት ስድስት ዓመታት የውስጥ አቅምን በመጠቀም በርካታ አስደናቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይሄንኑ ስኬት በማስቀጠል ኢኮኖሚያችንን ለማሻሻል ኢትዮጵያ አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በመስራት ላይ መሆኗን አስረድተዋል።   

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕያችንን በተሟላ መልኩ ልናሳካ የምንችለው የውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ እና የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

መንግስትን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ በጉባኤው ከወሰናቸው ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብና ማስተዳደር መሆኑን አያይዘው የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጠንካራ ፓርቲ፣ ፓርቲዉ የሚመራው ጠንካራ መንግስት እና ብልፅግናዉ የተረጋገጠ ማህብረሰብና ሀገር መፍጠር የሚቻለው ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ልማት ላይ ማዋል ሲቻል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለምዷዊዉ መንገድ የታቀዱ ዕቅዶችን ማሳካት እንደማይቻል ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለገቢ ሴክተር የተሰጠው ተልዕኮ የገቢ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ታዉቆ የውስጥ ገቢ አቅምን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ፍትሃዊና ተአማኒ ግብር ተሰብስቦ በአግባቡ ልማት ላይ ሊዉል እንደሚገባው በመርህ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑንና በተያዘው ዓመትም 75 በመቶ ወጪን በዉስጥ ገቢ የመሸፈን ዕቅድ ተጠናክሮ እንደሚሰራበት አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አመራሩ ህዝቡን አስተባብሮ ፍትሃዊ በሆነ አግባብ ገቢን በመሰብሰብ የልማት ስራዎችን በራስ አቅም በመሸፈንና የበልፀገ ማህበረሰብን በመፍጠር አሻራውን ሊያኖር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ተቋማዊ አደረጃጀትና የአሠራር ስርዓት ከመዘርጋት ባለፈ የገቢ ጉዳይ በየ 15 ቀኑ በአስተባባሪ ደረጃ መገምገም እንደሚገባው እንዲሁም ህዝቡን ባለቤት በማድረግ የመፈፀም እና የገቢ ስራው በህግ አግባብ ተፈፃሚ መሆኑን መከታተል እንደሚገባም አስረድተዋል።      

በክልሉ ገቢን ለመሰብሰብ ያሉ አመቺ ሁኔታዎችን በተለይም፡- የተዘረጉ የገቢ አሰባሰብ ህጎች፣ ሀገራዊ ፖሊሲ፣ የህዝብና መንግስት የመደጋገፍ ባህል መጠናከር እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።   

ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው የገቢ አሰባሰብ ስራውን በማጠናከር እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የግዴታ ወጪዎችን በራስ አቅም መሸፈን የሚገባ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ 

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው ቢሮው ለክልሉ የሀብት ምንጭ የሚሆን ገቢ በመሰብሰብ በበጀት ዓመቱ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸው፤ ከዕቅዱ 80 ከመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የኢኮኖሚ አቅምን በማሳደግ ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ ተቋማዊ አሰራርን በመፍጠር እና ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ አለምነሽ ገልፀዋል።

በበጀት አመቱ የህግና የአሰራር ማዕቀፎችን ለማሻሻል በተሰራው ስራም 7 አዋጆች በክልሉ ምክር ቤት የመጀመሪያ ጉባኤ፣ 5 ደንቦች በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት እንዲሁም 30 መመሪያዎች በቢሮው በኩል እንዲፀድቁ በማድረግ ቢሮው በስራ ላይ ማዋሉንም አብራርተዋል።

ወ/ሮ አለምነሽ በቀጣይ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የተቀመጡ የበጀት ዓመቱን የገቢ ግቦች ለማሳካት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልፀዋል። 

በተያዘው ዓመት በክልሉ ከ 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸው፤ ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ለገቢ ስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት እና በመቀናጀት በቁርጠኝነት በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የህግ ጥሰቶች የፈፀሙ 140 የገቢ አሰባሰብ ባለሙያዎች ላይ እንደፈፀሙት ጥሰት ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

አክለውም ከ 30 ሺ በላይ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በቴሌ ብር እንዲከፍሉ መደረጉን ጠቅሰው በ 2017 ሁሉም ግብር ከፋዮች በቴክኖሎጂ በተደገፈ አግባብ ግብር እንዲከፍሉ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በአዲሱ የበጀት ዓመት 12 ሺ የአዳዲስ ግብር ከፋዮች ምዝገባ ለማካሄድ መታቀዱንም ኃላፊዋ አሳውቀዋል፡፡

በጉባኤዉ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ የፓርቲና መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተካፋይ ሆነዋል።

Leave a Reply