የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንተርፕራይዞች ልማት እና የስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ “የክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል የ 2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ 2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።
መድረኩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ እና ወላይታ ዞኖች በደረሱ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ፀሎት በማድረግ ተጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ለዕድገትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው፤ ከጠንካራ መንግስት መገለጫዎች አንዱ የዜጎችን ጥያቄ በብቃት መመለስና ቃልን በተግባር ማሳየት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ብልፅግና ሰው ተኮር ፓርቲ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ለዜጎች ምቹ ሁኔታን በማመቻቸትና የክህሎት መር የስራ ዕድሎችን በመፍጠር የሌሎችን እጅ ሳያዩ ራስን በመቻል ለሌሎች መትረፍ የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት መርህ አድርጎ በመስራት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ ያሉንን ፀጋዎች በመለየት እና ብዝሃ ሀብቶቻችንን በአግባቡ በመጠቀም ለዜጎች ክህሎት መር የስራ ዕድል በመፈጠር ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚችል ዜጋን ለመፍጠር መስራት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው አመራሩ የስራ ዕድል ፈጠራን ቁልፍ የህልውና ጉዳይ አደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው አሳስበዋል።
ሁለንተናዊ ብልፅግናን አሳካለሁ ብሎ ለተነሳ መንግስት እና አመራር የስራ ዕድል ፈጠራ ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጠንካራ ተቋም በመፍጠር ለችግሩ ተቋማዊ ምላሽ ለመስጠት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ቅንጅታዊ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም በመግለፅ፤ ተቋማዊ አሰራሮችን በማሻሻልና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ሀገር የሚገነባ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል መፍጠር ይገባናል ብለዋል፡፡
በተለይ ግብርናን እና የቱሪዝም ዘርፉን ማዕከል ያደረገ የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለወጣቶች የመስሪያ ቦታ፤ ግባዓትና አጫጭር የክህሎት ስልጠና ዕድሎችን በማመቻቸት ለበርካታ ወጣቶች በሁለቱም ዘርፎች በርካታ የስራ ዕድሎችን ማመቻቸትና መፍጠር እንደሚቻል ገልፀዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ በተሟላ የአመራር ዑደት ዉስጥ ማለፍ እንዳለበት ገልጸው ተፈፃሚ የሚሆን ዕቅድ ማቀድ፣ ኦሬንቴሽን መስጠት፣ በተቀመጠው ጊዜ ማከናወን እና አፈፃፀሙን በቅርበት መከታተል መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የስራ፤ የአመለካከትና የአተያይ ባህል ለዉጥ ለማምጣት መስራት፣ ዉስብስብ ያልሆነ ቢሮክራሲ ተግባራዊ ማድረግ፣ ጤናማ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት መዘርጋት እንዲሁም በግብርና፣ ቱሪዝምና የዉጭ ስራ ስምሪት ያሉ ዕድሎችን አሟጦ መጠቀም በዘርፉ ጠቃሚ እርምጃዎች ናቸው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
ዜጎች መሠረታዊ ፍላጎታቸው ካልተሟላ በሂደትም ሆነ በዉጤት ቀዉስ ዉስጥ የመግባት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑንም ጠቁመው፤ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራን በሁሉም አካላት ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር ወደ ስራ መግባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ የዘላቂ ልማት እና የሠላም ዋስትና ማረጋገጫ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ባለድርሻ አካል በተለይም አመራሩ ከዕቅድ ጀምሮ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፈተሽና በመፍታት፤ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን በመቅረፅ እና ለወጣቱ ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር ለዉጤታማነቱ በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና የኢንተርፕራይዞች ልማትና ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ መድረኩ ጠንካራ አፈፃፀሞችን ለማስቀጠልና ድክመት የታየባቸውን ለማረም ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ 250 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉም በቀረበዉ ሪፖርት ተገልጿል።