በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም የተከሰተ ያልተጠበቀ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት የመላ ኢትዮጵያዊያንን ልብ የሰበረ፤ የክልላችንን ህዝቦች በፅኑ የሐዘን ዳዋ የመታ አስከፊ ጥፋት ደርሷል፡፡
አደጋውን ተከትሎ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዛሬ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ያወጀ ሲሆን፤ በእነዚህ ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች፤ በኢትዮጵያ መርከቦች፤ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል፡፡
በውሳኔው መሠረት በዛሬው ዕለት መላ ኢትዮጵያዊያን ከአደጋው ተጎጂዎች እና ከመላው የክልላችን ሕዝቦች ጋር ሐዘን ተቀምጠዋል፤ የሀገሪቱ ባንዲራም ዝቅ ብሎ በመውለብለብ ላይ ይገኛል፡፡
ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም የደረሰው ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋው የበርካታ ወገኖቻችንን ህይወት የቀጠፈ፤ ከአደጋው በሕይወት የተረፉትንም ወዳጅ ዘመድ ያሳጣ፤ እጅግ አስከፊ ጉዳት አስከተሏል፡፡
በዚያ ጥቁር ቀን እኚያ ደጋግ ወገኖቻችን የሐምሌ 15 ሰማይ ተደፍቶባቸው፤ ያረፉበት ምድር ከድቷቸው በቀን ጨለማ ተዋጡ፡፡
ለወትሮው ሰላም፤ ፍቅርና አብሮነት የሰፈነበት፤ የሰከነ ቀዬም በድንገተኛው አደጋ በለቅሶና ዋይታ ተቀይሮ ማቅ ለበሰ፡፡ ያ በጓሮው የሚኮተኩተውን፤ ለዕለት ጉርሱ የሚቀነጥሰውን የማያጣው ማህበረሰብ፤ በዛ የቀን ጎዶሎ የአፈር ክምር የለበሱ ወገኖቹን ፍለጋ ጭቃ የሚቧጥጥበት እጅግ ልብ ሰባሪ በሆነ አሳዛኝ ትዕይንት ተሞላ፡፡
በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የደረሰው አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ያስከተለው ጉዳት አስከፊና መራር በመሆኑ ወገኖቻችንን ለብዙ ህመም፤ ለብዙ መሰበር እና ለብዙ ማጣት ዳርጓቸዋል፡፡
አደጋው ያልነጠቃቸው ብቸኛው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ ደግነትን፤ በችግር ጊዜ ጥልቅ የመተሳሰብና የመረዳዳት ታላቅ ማህበራዊ እሴቶቻችንን ብቻ ነው፡፡
አደጋው ከደረሰበት ሰዓት ጀምሮ የአካባቢው ማህበረሰብን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያዊያን፤ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፤ የፌዴራልና የክልል መንግስታት፤ በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች፤ ተቋማት፤ አጋር ድርጅቶች፤ ባለሀብቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦች ሁሉም በታላቅ የወገንተኝነት ስሜት በአደጋው የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመርዳት ተስፋን የሰነቀ ተነሳሽነት አሳይተዋል፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አፋጣኝ የነፍስ አድን ምላሾችን በመስጠትና የሰብዓዊ ዕርዳታ በማቅረብ በሁሉም ወገን እየተደረገ ያለው ርብርብ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ፤ ምስጋና የሚቸረው ታላቅ የሰብዓዊነት ተግባር ነው፡፡
የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስትና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት አፋጣኝ የነፍስ አድንና የሰብዓዊ ዕርዳታ ከማድረግ ጎን ለጎን ማህበረሰቡን ከስጋት ቀጠና ውጪ በሆነ አግባብ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ሆኖም አደጋው በርካታ አባቶችንና እናቶችን ያለ ጧሪ፤ ልጆችና ህፃናትንም ያለወላጅ ያስቀረ እንዲሁም መላው ማህበረሰቡን ያለ ጥሪትና መጠለያ በማስቀረት ያፈናቀለ እና ለከፍተኛ ሰብዓዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የዳረገ በመሆኑ የመልሶ ማቋቋሙ ተግባር የሁሉንም ትብብርና የጋራ ርብርብ ይፈልጋል፡፡
በመሆኑም በየአካባቢው እና በተለያዩ ተቋማት የተጀመሩ ድጋፍ የማሰባሰብ ጥረቶችን አጠናክሮ በመቀጠል በአደጋው የተጎዱ ወገኖቻችንን በቋሚነት ለማቋቋም መረባረብ ይገባል፡፡
በተለይ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት 3 ተከታታይ ብሔራዊ የሐዘን ቀናት እንደ ሀገራችን ባህል ባለንበት እዝን በመድረስ በአደጋው ህይወታቸውን የተነጠቁ ወገኖቻችንን በፀሎታችን እያሰብን፤ ከአደጋው ተርፈው ለከፋ ቀውስ የተዳረጉትን በዘላቂነት ለማቋቋም እንደ ዜጋ የአቅማችንን በማድረግ ልናጽናናቸው ይገባል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ብር መተግበሪያ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም በ 8091 አጭር የመልዕክት ቁጥር አሊያም በቴሌብር ሱፐርአፕ ካቀረቡት ድጋፍ ማድረጊያ አማራጭ በተጨማሪ፡-
የክልሉ መንግስት እና የጎፋ ዞን አስተዳደር ለዚሁ ተግባር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፈቷቸው አካውንቶች በመጠቀም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአቅሙን አስትዋጽኦ እንዲያደርግ ሲል የክልሉ መንግስት በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ያስተላልፋል፡፡
*በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡- 1000641855239 (SER Geze Gofa Land slide victims)
*በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡- 1000511561276 (በጎፋ ዞን የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትና ምላሽ ፈንድ)፤
ለወገን ደራሽ ወገን ነው!!