ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዛሬው ዕለት በተከናወነው የሀገራዊው የአርንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 55 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ፤ ከዕቅድ በላይ 64 ሚሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉን በመግለፅ ለመላው የክልሉ ህዝብ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክተቻው ላቀድነው የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ ስኬት በክልሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ከማለዳው ጀምሮ በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት፤ በአንድ መንፈስ ወደ ችግኝ መትከያ ቦታዎች በመትመም ባደረጉት ርብርብ በአንድ ቀን 64 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በመርሃግብሩ በክልሉ በ713 ተከላ ጣቢያዎች ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሳተፋቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ትውልዱ ከጫፍ ጫፍ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ ቁርጠኝነቱን በተግባር በማሳየት አሻራውን ማኖሩን ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀማሪነት በ2011 ዓ.ም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በኅብረተሰባችን ዛፍ የመትከል ባህል መሰረታዊ ለውጥ በመታየት ላይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ደህንነቱ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለመጪው ትውልድ ማቆየት ይገባል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ከተባበርን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ መንፈስ ያቀድነውን ለማሳካት ከተረባረብን ምንም ነገር የሚያቅተን አለመሆኑን የዕለቱ የአንድ ጀንበር ተከላ አስደናቂ ስኬታችን ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ በሁሉም የልማት መስኮች በጀመርናቸው ስራዎች በአንድ መንፈስ በጋራ በመረባረብ የክልላችንን ልማትና የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የምናረጋግጥም ይሆናል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ በመላዉ የክልላችን ህዝቦች ጽናት እና ትጋት ለተመዘገበው ስኬት በማስተባበርና በመምራት ጉልህ አስትዋጽኦ ላደረጉ እንዲሁም ከማለዳ እስከ ምሽት በትጋት ለተከሉ በሙሉ ልባዊ ምስጋናቸውን በማቅረብ በቀጣይ የተተከሉትን በመንከባከብና በመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ ራዕያችንን ዕውን እናድርግ ብለዋል፡፡