ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት “የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራትና ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ያዘጋጀው የትምህርት ጉባኤ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ያቀድነውን ብልፅግና ለማረጋገጥና የበለፀገ ኅብረተሰብ ለመገንባት ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባል ብለዋል።
ብቃት ያለው ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት የሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ እና ብቃት ባለው የትምህርት አስተዳደር የሚመራ ትምህርት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው የክልሉ መንግስት ከክልሉ ምስረታ ማግስት ጀምሮ ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረው፤ በዚህም በዘርፉ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልፀዋል፡፡
ትምህርት የአንድ ወገን የስራ ድርሻ ሳይሆን የሁሉም የጋራ ማህበራዊ ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለትምህርት ዘርፉ ወጤታማነት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እና አመራር ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ሰብሰብ ብለን ከሰራን ውጤት ማምጣት እንችላለን ሲሉ አስገንዝበዋል።
አክለውም በተለይ ህዝቡን በትምህርት ዘርፉ በንቃት ማስተባበርና ማሳተፍ ከቻልን ባጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ስኬት ማስመዘግብ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በመንግስት እና በግል ትምህርት ቤቶች ያለውን ልዩነት ማጥበብ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ ጉባኤውም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄን ስናደርግ ኢትዮጵያን በብቃት መምራት የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት እንችላለን ብለዋል።
መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ የትምህርት ምገባ ስራን ኅብረተሰቡን በማሳተፍ አጠናክሮ መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የትምህርት ቤት ምገባን በ2016 ከነበረው በእጥፍ ማሳደግ የሚገባ መሆኑንም ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ካለፈው በጀት ዓመት ውስንነቶችን በማሻሻል በ2017 የብልፅግና ተምሳሌት ክልል ለመፍጠር በምናደርገው ጥረት በትምህርት ዘርፍ በትኩረት መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ብለው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል፡-
*የትምህርት አስተዳደርና ውጤታማነት በተመለከተ፡-
የትምህርት ዘርፉ ውጤታማና ፍሪያማ በሆነ መንገድ ብቃት ባለው የትምህርት አስተዳደር እየተመራ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶችን ውጤታማ የሚያደርግ አመራር ለዘርፉ ውጤታማነት ቁልፍ ሚና መጫወት ይችላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የትምህርት አመራሮች ጠባቂ ሳይሆኑ የመፍትሄ ባለቤቶች ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከውጤት ጋር ተያይዞ በክልሉ እየተመዘገበ ያለው የተማሪዎች ውጤት ካምናው መሻሻሎችን ያሳየ ቢሆንም በቀጣይ የተማሪዎቻችንን ብቃት በማሳደግ በተገቢው መንግድ አዘጋጀቶ ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ ለማስቻል ያሉ ችግሮችን ለቅሞ በመለየት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
*የመምህራን አቅም ግንባታ በተመለከተ፡-
ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ወሳኝ ከሆኑ ተግባራት አንዱ የመምህራን አቅም ግንባታ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ትኩረት ሰጥቶ በክልሉ ያሉ የተለያዩ ተቋማትን በመጠቀም የመምህራንን አቅም ለመገንባት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አክለው በመምህራን መመዘኛ ፈተና ላይ የታየው ማሽቆልቆል ብቃት ያለው መምህር ከማፍራት አኳያ ብዙ ስራ እንደሚጠበቅብን ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ጉዳይ ከመምህራን ጋር ቀረብ ብሎ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
*ከትምህርት ግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ፡-
ከትምህርት ግብዓት አቅርቦት አኳያ ያሉ ችግሮችንና ውስንነቶችን ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ወላጆች እና ባለድርሻ አካላት በዚህ ክረምት ትምህርት ቤቶቻችን ምን ይመስላሉ ብለው በመመልከት የጎደለውን የማሟላት ኃላፊነት በመውሰድ የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን፤ በተለይ በተያዘው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች በትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።
አያይዘው በክልላችን በቅርቡ በየደረጃው ባሉ የትምህርት ዕርከኖች የጋጠመን የመፅሐፍት ዕጥረት ለመቅረፍ አንድ መፅሃፍ ለአንድ ተማሪ በሚል ሀሳብ ለመጻህፍት ህትመት ሀብት የማሰባሰብ ዘመቻ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልፀው፤ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የታተሙ መጽሐፍት በአግባቡ ለተማሪዎች ተደራሽ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በተጀመረው የአንድ መፅሃፍ ለአንድ ተማሪ ኢኒሼቲቭ ላይ ለተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልባዊ ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የትምህርት ጥራት ተከታታይ ድጋፍና ጥረቶችን የሚፈልግ በመሆኑ ይህን መልካም ተሞክሮ በማስፍት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለትምህርት ዘርፉ ውጤታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና የጋራ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት በመግለጽ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መምህራን፣ የትምህርት አስተዳደሩ፤ አመራሩ፤ ወላጆች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በ2017 የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከትና በቅንጅት በመስራት የትምህርት ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንዳለበቸው አሳስበዋል።