ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን፤ ገዜ ጎፋ ወረዳ በከንቾ ሻቻ ጎዝድ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች፤ ቋሚ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በዛሬው የጳጉሜ 1 የመሻገር ቀን በዞኑ በቡርዳ ቀበሌ ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ለአደጋው ተጎጂዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የተጀመረው በአደጋው ውድ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የአንድ ደቂቃ የሂሊና ፀሎት በማድረግ ነው፡፡
በጎፋ ዞን የደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ፤ የበርካታ ወገኖች ህይወት መቅጠፉ እና ከ600 በላይ አባወራዎችን ማፈናቀሉ ይታወሳል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ጥላሁን ከበደ የመኖሪያ ቤት ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ክልላችንን አዲስ ክልል በአዲስ ዕሳቤ በሚል መስርተን፤ ሙሉ ትኩረታችንን ወደ ልማት በማዞር ክልሉን ለማሻገር አቅም የሚፈጥሩ ስኬቶች በማስመዝገብ ላይ በነበርንበት ወቅት ያገጠመን አደጋ፤ እጅግ ልብ ሰባሪና ፈታኝ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
አደጋውን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለተጎጂዎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች በተደራጃ መልኩ አስፈላጊ ድጋፎች ከማድረግ ባለፈ፤ ዋነኛ ትኩረቱን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ላይ በማድረግ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው የመሻገር ቀንም ከሐምሌ 15 የጥፋት ጽልመት ወጥተን፤ በአደጋው የተፈናቃሉ ወገኖች ከአደጋ ስጋት ቀጠና ውጪ በሆነ አካባቢ በቋሚነት መልሶ በማቋቋም ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ ወሳኝ እርምጃ የሆነው፤ ቋሚ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በይፋ ለማስጀመር በቅተናል ብለዋል፡፡
ኅብረት አንድነታችንን አጠንክረን ተባብረን ከሰራን የትኛውንም ችግር መሻገር እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአንድ ቀን የ100 አባወራ እንዲሁም በአንድ ሳምንት የ600 ቤት ግንባታ ለመጨረስ በማቀድ ስራ የጀመርነው ኅብረታችንን በመተማመን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው አደጋውን ተከትሎ መላ ኢትዮጵያዊያን፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላት ተጎጂዎችን ለመደገፍ ያደረጉት ርብርብ ተስፋ የሰጠንና ለዛሬው ዕለትም ያበቃን ነው በማለት የመተባበርን ዋጋ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
ዕለቱ “የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ፤ የመሻገር ቀን በሚል በመላ ሀገሪቱ በመከበር ላይ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችን በአዲስ መልክ መልሶ በማቋቋምና ወደ ቀደመ ህይወታቸው በመመለስ አስቸጋሪውን ጊዜ እንሻግራለን ብለዋል፡፡
የዛሬው የጳጉሜ 1 የመሻገር ቀንንም በአስከፊው አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የመኖሪያ ቤት በመገንባት ተግባር እናሳልፋለን ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም በየአካባቢው ዕለቱን በሚያሻግሩ በጎ ተግባራት እንዲያሳልፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ተጎጂዎችን በተለያየ መልክ ለረዱ፤ የሰብዓዊ ዕርዳታ በማቅረብ ለደገፉ እና የመልሶ ማቋቋም ጥረቱን በማገዝ ላይ ላሉ ሁሉ በመላው የክልሉ ህዝብ እና መንግስት ስም ከፍ ያለ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
ተጎጂዎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራው የመኖሪያ ቤት ከመገንባት ባለፈ፤ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማሟላት፤ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ፤ የእርሻ ቦታዎችንና ቋሚ የኢኮኖሚ መሰረቶችን ማመቻቸትን የሚያካትት መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ርብርቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡