በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይገባል፦ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በጋሞ ዞን ዳራማሎ ወረዳ የስራ ጉብኝት በማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚሁ የስራ ጉብኝት ዳራማሎ ሲደርሱ በአካባቢው ህብረተሰብ እና በወረዳው አስተዳደር ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዳራማሎ ቆይታቸው በተለይ የሉና ኤክስፖርት ቄራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተቀናጀ እርሻ ልማትን ጎብኝተዋል፡፡

ድርጅቱ የሉና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እህት ኩባኒያ ሲሆን፤ በእርሻ፤ በእንስሳት ልማት እና መኖ ምርት በመሰማራት በተቀናጀ እርሻ ልማት ዘርፍ በማልማት ላይ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ በ447 ሄክታር መሬት ላይ አትክልት፣ ቋሚ ተክል፤ የእንስሳት መኖ እና ከብት ድለባ ላይ ተሰማርቶ የተቀናጀ የግብርና ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ተመልክቷል፡፡

ድርጀቱ በተለያዩ የስራ ዘርፎቸ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ ከመሆኑም በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለሀገር ልማት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የፕርጀክቱን የመኸር እርሻ ስራ እና የሌማት ትሩፋት ተግባር ውጤታማነት ለመከታተልና ድርጅቱ በአካባቢው በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለመመልከት መሆኑን ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው፤ የሉና የተቀናጀ የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት፤ በተለይ ለሌማት ትሩፋት ተግባራችን ማነቆ የሆነውን የእንስሳት መኖ ከማምረት ባሻገር፤ በተቀናጀ እርሻ ለሀገር ተሞክሮ የሚሆን ተግባር እያከናወነ መሆኑን በመስክ ጉብኝቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሉና የተቀናጀ ግብርና በተለይ በሰብል ልማት፣ በእንሰሳት እርባታ እና መኖ ልማት በዘመናዊ መንገድ እጅግ ዉጤታማ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል። 

በአካባቢው በኩታ ገጠም አስተራረስ ዜዴ ተጠቅመው፤ አካባቢዉን ዘመናዊ የግብርና ተሞክሮ ማዕከል በማድረግ የተፈጥሮ ፀጋን ተጠቅመዉ ወደ ባለፀጊነት እየተቀየሩ የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች መፈጠራቸውን ገልፀው፤ ይህንን ተሞክሮ በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች በማስፋፋት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እንረባረባለን ብለዋል።

የግብርናው ዘርፍ ውጤታማነት ወደ ብልፅግና ለሚደረገው ሽግግር ቁልፍ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ፤ በክልሉ በግብረና ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 95 ሺህ ሄ/ር የእረሻ ማሳ የተሰጠ መሆኑን ተናግረው፤ ከዚህ ውስጥ 54 ሺህ ሄክታሩ መልማቱን አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዳራማሎ ወረዳ በነበራቸው የስራ ቆይታ፤ በወረዳው በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኘውን የዋጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል፡፡

ለሀብት አሰባሰብ ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በመቀስቀስ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማድረግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።

እስካሁን ለሆስፒታሉ ግንባታ 41 ሚሊዮን ብር ከህብረተሰብ ተሳትፎ መሰብሰቡ ታውቋል።

Leave a Reply