የክልሉ መንግስት የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በማድረግ ላይ ባለው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ በመምጣት ላይ ይገኛል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

የኢፌድሪ የጤና ሚንስቴር “የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ እምርታ ለተፋጠነ የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በአርባ ምንጭ ከተማ 26ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤውን አካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጉባኤውን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱ ሲሆን፤ በንግግራቸው 26ኛውን የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ የምክክር ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ምድረ ገነቷ አርባ ምንጭ ከተማ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ፣ በወላይታ እና በጋሞ ዞኖች ባለፈው ዓመት በተከሰቱ የመሬት መንሸራተት የተፈጥሮ አደጋዎች አስከፊ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው፤ የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ እና መልሶ ለማቋቋም በተደረገው ጥረት የጤና ሚንስቴር እና የአጋሮቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ለተደረገው  ድጋፍ በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተመሰረተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በማህበራዊ፤ በኢኮኖሚያው እና በህዝብ አስተዳደር ዘርፍ የተወጠኑ ግቦችን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ተጨባጭ ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት በተለይ ለማህበራዊ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ ክልሉ በተመሰረተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የክልሉን ህዝብ ጤና ለማሻሻል የሚያግዙ የጤና መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት እና የተጀመሩትን የማጠናቀቅ ስራ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በስፋት መስራቱንም አብራርተው፤ በዚህም ለውጥ እየመጣ መሆኑን  ገልጸዋል።

ሆኖም አገልግሎቱን የተሟላ ለማድረግ ተቋማትን በአስፈላጊው ግብአት ለሟሟላት በሚደረገው ጥረት የጤና ሚኒስቴር እና አጋሮች ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።    

መከላከል ላይ የተመሠረተው የጤና ልማት ሥራ በተለይ በጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት መሻሻሎች ቢኖሩም፤  የጤና ኤክስተንሽን ስርዓቱ የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ ወባን ጨምሮ ሌሎች ወረርሽኞች አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈሉ የሚገኙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይ የጤና ኤክስተንሽን ስርዓቱን በማጠናከር እና የአቅም ማጎልበት ስራዎችን በመስራት ጠንካራ የበሽታ መከላከል ስርዓት መዝርጋት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረው፤ በዚህ ረገድ ሚኒስቴር መ/ቤቱን ጨምሮ የሚመለከታችው አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም ዜጋ የጤና አገልግሎት የማግኘት ሰብአዊ መብት እንዳለው የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የውስጥ አቅማችንን በማስተባበር የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎትን በክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ ለማድረግ በተደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።     

ሆኖም ከመድኃኒት አቅርቦት ውስንነት ጋር በተያያዘ በአገልግሎቱ ክፍተት መኖሩን በመጥቀስ፤ መድኃኒት አቅርቦት ላይም ሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የሚመለካታቸው አጋር አካላት ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን ምርታማነትን በማሳደግ እና ከተረጅነት በመላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት በመመዝገብ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግስት በምግብ እጥረት የሚመጣውን ትወልድ ተሻጋሪ አደጋ ለመቅልበስ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ማዕክል አድርገው የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ይህን የክልሉን ጥረት በማገዝ ከክልሉ ጋር አብረው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋንና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ሚኒስትሯ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የመካከለኛው ዘመን የጤናው ዘርፍ ልማት በማጠናከር ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋንና ጥራት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው፤ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከ16 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ እናቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ መደረጉንም ጠቁመው፤ የህፃናት ጤናን ለማሻሻል የክትባት አገልግሎት፣ የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት ህክምና አገልግሎት የተሳካ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የወባ በሽታን ለመከላከል በማህበረሰብ ንቅናቄ ከኬሚካል ርጭትና አጎበር አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር በተጨማሪ ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን በማዳፈንና በማፋሰስ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከማህፀን በር ካንሰር ልየታ ጋር በተያያዘ ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 49 የሚሆኑ 687 ሺህ ሴቶች ልየታ ተደርጓል ብለዋል።

ሁሉ አቀፍ የጤና ስርዓታችንን በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ የዲጂታል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤  በዚህም አበረታች ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

የመድሃኒትና የህክምና መሣሪያዎች አቅርቦትን ለማሻሻል ከ77 ቢሊዮን በላይ ብር በሆነ ወጪ ግዥ ተፈጽሞ መሰራጨቱን ገልጸው፤ ዘርፉን የማጠናከሩ ተግባር መቀጠሉን አብራርተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመካከለኛው ዘመን የጤና ዘርፍ ልማት ዕቅድ ለማሳካት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ገልጸዋል።

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል፣ የህብረተሰብ ጤና አገልግሎትን ለማጠናከር የግሉን ዘርፍ ያካተተ ተግባር እየተፈጸመ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ስራን በተቀናጀ መንገድ በማከናወን የጤና መሪ ዕቅድን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

Leave a Reply