የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው የኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል የብሩህ ተስፋ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የዘንድሮውን በዓል የምናከብረው ለሀገራዊ እና ክልላዊ የሰላምና የብልጽግና ራዕዮቻችን ስኬት፤ በሁሉም መስክ በህዝባችን ባለቤትነት በተመዘገቡ ውጤቶች የሚጨበጥ ተስፋን ይዘን፤ የመጪዉን ብሩህ ዘመን አሻግረን እያየን ነው በማለት ገልጸዋል። የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-  

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ፤ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!   

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የድኅነታችን የተሰፋ ቃል የተፈጸመበት፤ ዓመተ ኩነኔ ተደምስሶ፤ ዓመተ ምሕረት የታወጀበት ዕለትን በማሰብ በድምቀት የሚከበር፤ የክርስትና አስተምህሮ መሠረት የሆነ ታላቅ በዓል ነው፡፡ 

በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ይህ በዓል፤ የብሩህ ተስፋ መገለጫ ነው፡፡ የክርስቶስ መወለድ ጨለማው በብርሃን የመሸነፉ ምልክት፤ የብሩህ ዘመን ማብሠሪያ ነው።

የዘንድሮውን የገና በዓል የምናከብረው፤ ለሀገራዊ እና ክልላዊ የሰላምና የብልጽግና ራዕዮቻችን ስኬት፤ በሁሉም መስክ በህዝባችን ባለቤትነት በተመዘገቡ ውጤቶች የሚጨበጥ ተስፋን ይዘን፤ የመጪዉን ብሩህ ዘመን አሻግረን እያየን ነው።

ፍጡርና ፈጣሪ አንድ የሆኑበት በዓለ ልደቱን ስናከብር፤ ከነሄሮድስ የኃይል፤ የሸፍጥ፤ የጦረኝነት፤ የጥላቻና የጥፋት መንገድ ይልቅ፤ በክርስቶስ የፍቅር፤ የይቅርታና የሰላም መንገድ ቂም፤ ቁርሾና በቀልን በይቅርታ በመሻገር ሊሆን ይገባል፡፡  

በእምነቱ አስተምህሮ መሠረት፤ የክርስቶስ ልደት የልዩነትን ግንብ ያፈረሰ፣ የጠብን ግድግዳ የናደ፣ የጥላቻን መጋረጃ የቀደደ እና የተለያዩትን አንድ ያደረገ ነው፡፡

በመሆኑ ከትዕቢት ይልቅ ትህትናን ገንዘባችን በማድረግ ከጥላቻ እና ከመከፋፈል መንገድ ተላቀን በፍቅር፣ በመደመር እንዲሁም በአብሮነት እና በመተጋገዝ ክልላችንን የሰላም፤ የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የሰነቅነውን ራዕይ እውን ለማድረግ  መትጋት ይገባናል።

በዓሉን ስናከብር በህዝባችን ዘንድ ለዘመናት የገነባነውን የመቻቻል፣ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት በማጎልበት፤ ጊዜያዊ ፈተናዎችን በፅናት እያለፍን፤ በጋራ የሰነቅናቸው ግቦችን ዕውን ማድረግ እንደምንችል በማሰብም ጭምር ሊሆን ይገባል።  

የገና በዓል የትህትና ሚስጢር የተገለጠበት፤ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፤ በከብቶች በረት ተወልዶ ፍፁም ትህትናንና ፍቅርን ያስተማረበት ነው፡፡

እኛም ከኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ትህትናን በመማር፤ በየተሰማራንበት መስክ ክልላችንና ህዝባችንን በፍጽም ትህትናና ቅንነት ለማገልገል በመነሳት ሊሆን ይገባል፡፡

አንድነትና ኅብረት፤ መደጋገፍና መረዳዳት በክርስትና ልዩ ስፍራ እንደሚሰጠው የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በዓሉን በመተሳሰብና በመጠያየቅ፤ ያለንን ለለሌው በማካፈል፤ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማቋቋም በመተባበር እንዲከበር ስል አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡ 

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።

በድጋሚ መልካም የልደት በዓል ይሁንልን!

ፈጣሪ ሀገራችንን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!!

Leave a Reply