በአለማችን ከከፍተኛ የደን ሽፋን መመናመን፤ ከተጥሮ ሀብት አያያዝ እና ሌሎች በርካታ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የሰው ልጅ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ እና በተፈጥሮ አደጋዎች እየተፈተነ ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድ የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል መንግስት ለአካባቢ ጥበቃና ለአረንጓደ ልማት ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በክልሉ ደህንነቱ የተረጋገጠ አረንጓዴ ከባቢን ዕውን የማድረግ ክልል አቀፍ ስራዎች፤ ከሀገራዊ ፖሊሲ እና ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በተናበበ መልኩ ገቢራዊ በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአካባቢ ጥበቃ ካለው ዘርፈ ብዜ ጠቀሜታ አንጻር፤ ከመደበኛ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፤ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች በተጨማሪ፤ ለተራራ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት “በአንድ ዞን አንድ ተራራ መልሶ የማልማት” ክልላዊ ኢንሸቲቪ ማስተዋወቃቸው ይታወሳል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አርባ በመቶ የሚሆነው ክፍል ተራራማ በሆነው ክልሉ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ከተራቆተ የተራራ ስነ ምህዳር ጋር ተደምሮ የደቀነውን ስጋት በመገንዘብ፤ በ 12ቱም ዞኖች የሚለሙ የተራቆቱ ተራሮች ካርታ ለየዞኑ በማስረከብ መልሶ የማልማት ስራውን ማስጀመራቸውም ይታወቃል፡፡
ኢንሼቲቩ የተራቆቱ ተራሮችን መልሶ በማልማትና የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ ተፈጥሮን ለትውልድ የማቆየት ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት ሊከናወን እንደሚገባ ማሳሰባቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ለኢንሼቲቩ ተግባራዊነት ህብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ እንዲሁም በክልሉ ደን አከባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ሙያዊ ድጋፍ ታግዞ የተቀናጀ ርብርብ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም በ12ቱም ዞኖች 4350 ሄ/ር የተራቆቱ ተራሮች ሥነ ምህዳር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባላቸው የደንና የፍራፍሬ ችግኞች መልሶ የማልማት ተግባር ውጤታማ በሆነ መንገድ በመከናወን ላይ ሲሆን፤ በክልሉ ተራሮች የስጋት ምንጭ ሳይሆኑ የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ ለማስቻል በመሰራት ላይም ነው፡፡
የተራራ ልማት ኢንሸቲቩን ከሌሎች መርሃ ግብሮች በተለይም ከመደበኛው የአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም ከሌማት ቱርፋት የንብ ሀብት ልማት ጋር በማስተሳሰር በተተገበረባቸው የተሻለ ውጤታማነት መመዝገቡም የተመለከተ ሲሆን፤ ይህንኑ ማስፋትና አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡
ከዚህም ባሻገር በክልላችን ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የተራሮች መሠረታዊ መረጃዎች በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ የመሰብሰብና የማጠናቀር ስራ በመሰራት ላይ ሲሆን፤ ይህም አገራችን ለካርበን ሽያጭ የጀመረችውን ሥራ የምያሳልጥ ይሆናል።
በአጠቃላይ በክልሉ በመከናወን ላይ ያሉ የተራራ ልማትና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች፡-
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፤ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን ለመከላከል፤ የውሃና ብዝኃ ሕይወት ሀብትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ከባቢና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ቀጣይነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።