እንደ “ዎና” ያሉ የጎላ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ የህዝቦች አንድነትን ለማጠናከር እና ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ታሪክ ለማድረግ መጠቀም ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት “ዎናንካ አያና” የቡርጂ ብሄረሰብ የምስጋናና የዘመን መለወጫ የ “ዋናንካ አያና” በዓል “የዎና በዓል ለሰላም፤ ለአብሮነት እና ለብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በቡርጂ ዞን፤ በሶያማ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የዎናን በዓል ከመላው የቡርጂ ማህበረሰብ ጋር በአንድነትና በአብሮነት ለማክበር ቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ ሲደርሱ፤ በዞኑ አስተዳደርና በአካባቢው ማህበረሰብ ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክብረ በዓሉ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት:-ቡርጂ ዞን እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ፀጋ የታደለ ዞን ነው ቡርጂዎች ደግሞ ፀጋችሁን ጠብቃችሁ መቆየት ልምድ ያላችሁ ናቸው ብለዋል።

በዓሉ ከግብርና ጋር የተቆራኘ ህይወት ያለው ታታሪው የቡርጂ ህዝብ ምርት ሰብስቦ፤ አመቱን ለፍቶ የዘራው አዝመራን ለፍሬ ላበቃ ፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት እና ለቀጣይ የበልግ አዝመራ ዝግጅት በአዲስ ጉልበት የሚነሳበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ የስራ ወዳድነትና የጠንካራ የስራ ባህል መገለጫ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡  

የዎና በዓል የቡርጂ ማህበረሰብ በሚታወቀው የግብርና ስራ በላቡ ጥሮ ግሮ አካባቢውን በመቀየር ከድህነት እንዲወጣ ጠንካራ የሥራ ባህልን የሚያሰርጽ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህን ድንቅ ዕሴት ጠብቀው ላቆዩ አባቶች ምስጋና ይገባል ብለዋል፡፡

ቡርጂዎች የሚታወቁት በአምራችነታቸው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቡርጂዎች የሚታወቁበት ከነጭ ማኛ ጤፍ እስከ ቦሎቄ የሚያመርት፤ ህዝቡም ከእርሻው የማይለይ ትጉህ ህዝቡ መሆኑን በመግለፅ ይህን ባህል አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አክለው ዎና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፣ የበዓሉን እሴት ጠብቆ በአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ታሪክ ለማድረግ መጠቀም ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል። 

በዓሉ ማህበራዊ ፋይዳውም ጥልቅ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የተራራቁና የተነፋፈቁ የሚገናኙበት፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶች ያሉት፣ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በወንድማማችነት የሚከበር የመደመር ዕሳቤ ተምሳሌት የሆነ ድንቅ በዓል ነው ብለዋል።

በዓሉ የሰላም፤ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴት:- የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ እና ነጠላ ከፋፋይ ትርክቶችን በመታገል ገዢ ትርክትን በማስረፅ፣ እንዲሁም ወቅታዊ ችግሮችን በጋራ በመሻገር ለጋራ ልማትና ብልፅግና በህዝቦች መካከል ኅብረት እና ትብብር የሚያጎለብት መሆኑንም ገልፀዋል።

ቀጠናው ከዚህ ቀደም የግጭት ነጋዴዎች ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩበት አካባቢ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቡርጂ ማህበረሰብ እና አባቶች ሰላምን አስጠብቃችሁ በማቆየታችሁ ሰላም እንዲረጋገጥ ሆኗል ብለዋል።

አክለው ፍቅር፣ መተሳሰብ እና አንድነት ካለ ነገ የተሻለች ደቡብ ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ቡርጂዎች ተፈጥሮን በመጠበቅ፤ በተለይ በሀገር በቀል እውቀት የአፈርና ውሃ መሸርሸርን በመከላከል በአስቸጋሪ መሬት ጭምር በማምረት የሚታወቁ ናቸውም ብለዋል፡፡

እንደ ማህበረሰብ ይህን ተሞክሮ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠንሳሽነት፤ በሀገር ደረጃ በመተግበር ላይ ካለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ጋር በማስተሳሰር እና በማስፋት በአካባቢው የተራቆቱ ተራሮችን መልሶ በማልማት ምሳሌ ሊትሆኑ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝቡ የበዓሉን የሰላም፣ የመተባበርና የመተጋገዝ እሴት እና ጠንካራ የስራ ባህል ተጠቅሞ፣ በህብረት ሁለንተናዊ ብልጽግናውን ለማረጋገጥ ተግቶ በመስራት ቡርጂን በበርካታ የልማት አውታሮች የምትታወቅ እትዲትሆን የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለፅ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

በሌላ በኩል ርዕሰ መስተዳድሩ በቡርጂ ቆይታቸው በሶያማ ዙሪያ ወረዳ፤ በገመዮ ቀበሌ የድንጋይ ከሰል የማምረት ሥራን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

Leave a Reply