ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት አመት የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት አቀረቡ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል፡፡

በጉባኤው የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት አመት የግማሽ አመት ዕቅድ አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው የክልሉ መንግስት የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ፤ ፀጋና እምቅ የመልማት አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የ2017 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፤ በግማሽ የበጀት ዓመቱ በአስፈፃሚ ተቋማት የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ሰፊ ርብርብ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ 

በተለይ በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ሪፎርም በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ህዝቡን ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በግማሽ አመቱ በሁሉም አውታሮች በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት 6 ወራት የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ስኬት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በሁሉም የልማት መስኮች አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በግማሽ አመቱ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና በክልሉ የተረጋጋ ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በራስ አቅም ምላሽ ከመስጠት አንጻር ዕምርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር የታሪክ እጥፋትን ለማስመዝገብ በሚያስችሉ ዘርፎች በተለይም በሰብል ልማት እና በቡና ስፔሻላይዜሽን ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

አክለው በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ስራዎች፤ በሆርቲካልቸር ልማትና በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቪ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን የመቀነስና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም አመርቂ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይ በትምህርት ለትዉልድ ንቅናቄ የግብዓት አቅርቦትን የማጠናከር፣ የጤና መድህን ሽፋንን የማሳደግ፤ የወባ ወረርሽኝን የመከላከል እና የጤና ግብዓት ችግሮችን የመቅረፍ ውጤታማ ተግባራት ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡

አያይዘው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የማጠናከር፤ በተሳለጠ የግብይት ሥርዓት ምርትን ለገበያ የማቅረብ፣ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን የማዘመን፣ የከተሞችና የኢንዱስትሪ ልማትን የማፋጠን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮች ተደራሽነት እንዲሁም የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ተሳትፎን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

በአንጻሩ የገበያ ማረጋጋትና የዋጋ ንረትን የመቆጣጠር ውስንነት፣ የነዳጅ አቅርቦትና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ኮንትሮባንድ እንዲሁም ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን የመሰብሰብ የዉጤታማነት ችግር በግማሽ የበጀት አመቱ ከታዩ ድክመቶችና ተግዳሮቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡  

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በዋና ዋና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች፡- በግብርና፤ በሰላምና ፀጥታ፤ በትምህርትና ጤና፤ ኢንቨስትመንት፤ መሰረተ ልማት፤ ስራ ዕድል ፈጠራ፤ ገቢ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ዘርፍ በግማሽ የበጀት አመቱ በተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች ላይ በማተኮር ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡  

በግብርናው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት፤ በበልግና መኸር የተሻለ ምርት መገኘቱ በሪፖርቱ የተዳሰሰ ሲሆን፤ በፍራፍሬ ምርት በክላስተር የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ዉጤት የታየባቸው መሆኑ እንዲሁም ክልሉ ካለዉ ሰፊ መሬት አንፃር ምርታማነትን ከዚህ በላይ ማሻሻል በቀጣይ ይበልጥ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ለማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይ ለትምህርት እና ጤና ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎች መስራቱንና አበረታች ውጤት ማግኘት መቻሉም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በጤናው ዘርፍ በተለይ በጤና ተቋማት ግንባታና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሁም የወባ በሽታ ስርጭትን በመቆጣጠርና በመከላከል፤ በጤና መድህን እና በህብረተሰብ ጤና በርካታ ስራዎች ተሰርተው አበረታች ውጤት መመዝገቡ በርፖርቱ ተዳሷል።

በትምህርት ዘርፍ በበጀት አመቱ በሁሉም ዕርከኖች የትምህርት ተደራሽነት፤ ፍትሀዊነት እና ጥራት የማስጠበቅ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ለቀጣይ መሰረት የጣሉ ውጤቶች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ በበጀት አመቱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች በጥቅሉ ከ4.7 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 157 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን ከ45 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውም ተጠቁሟል፡፡

በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች፡- በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች የግል ሀብታቸውን በመጠቀም ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ ፕሮጀክቶች የሚገኙበትን የአፈፃፀም ደረጃ ለማወቅ በተሰራ ሥራ 511 ፕሮጀክቶች የሚገኙበትን ወቅታዊ ደረጃ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም በገቡት ውል መሠረት እያለሙ ባልሆኑ 32 ፕሮጀክቶች ላይ የጽሁፍ እንዲሁም በ79 ፕሮጀክቶች ላይ የቃል ማስጠንቀቂያ በህጉ መሰረት የተሰጠ ሲሆን በድምሩ በ111 ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዱን ተናግረዋል።

የክልሉን ገቢ ከማሳደግ አኳያ በበጀት አመቱ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ፤ የክልሉን የበጀት ፍላጎት 57 በመቶ በውስጥ ገቢ ለመሸፈን ታቅዶ፤ በግማሽ የበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉም ተገልጿል፡፡ ይህም ከእቅዳችን አኳያ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ አንዳለብን ያመላክታል።

ግብር ከመሰብሰብ አንጻር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ከመሰብሰብ፤ ግብር ከፋዩም ግዴታውን አውቆ ከመክፈል አንጻር፤ ሰፊ ስራ ይጠበቅብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ ምክርቤት አባላት የክልሉ ታክስ አምባሳደሮች እንደመሆናቸው በየተወከላችሁበት ምርጫ ክልል ፍትሃዊና ተኣማኒ የሆነ ታክስ እንዲሰበሰብ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በተለይም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ልየታና ግንዛቤ ፈጠራ አንፃር የተሠሩ ስራዎች አበረታች ውጤት የታየባቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በክልሉ የሚገኙ እንደ ሆስፒታል ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉ፤ በአጠቃላይ 55 ፕሮጀክቶች በጀት ተይዞ ወደ መጠናቀቁ ምዕራፍ እየመጡ መሆናቸው በሪፖርቱ ተዳስሶ፤ በበጎ ጎኑ ተቀምጧል።

የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት ችግርን ማሻሻልና ለዉጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማሳደግ፤ በዞኖች የኮሪደር ልማትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር፣ ማዴያዎች በቴሌብር እንዲጠቀሙ የተጀማመሩ ስራዎች አበረታች እንደሆኑም ተመላክቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከከተሞች ልማት ጋር በተያያዘ፤ በተለይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሀሳብ ጠንሳሽነት ከሚተገበረው የኮርደር ልማት ተግባር አኳያ በክልሉ ባሉ ከተሞች በዎላይታ ሶዶ፤ አርባ ምንጭ፤ ዲላ፤ ካራት፤ ጂንካ፤ ሣውላ፤ ይርጋጨፌ፤ ጊዶሌ እና ኬሌ ከተሞች፤ በኮርደር ልማት 41 ኪሜ፤ 26 ሄ/ር የአርንጓዴ ፓርክ ልማት፤ የልጆች መጫወቻ፤ አደባባዮች እና ሌሎች አገልገሎት ሰጪ ተቋማት መገንባት መቻሉን ገልፀዋል።

በዚህም የከተማ ነዋሪዎች፤ የተለያዩ ባለሀብቶች፤ ምሁራን እና ባለሙያዎች ይህንን ልማት በመደገፍ፤ በመከታተል እና የራሳቸው አድርገው በልማቱ በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ተናግረው፤ ለዚህ የተከበረው ምክር ቤት ዕውቅና አንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ከባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ልማት ጋር ተያይዞ፤ በተለይ የተፈጥሮ መስህቦች ጥበቃና ልማትን ለማሳደግ 18 አዳዲስ የተፈጥሮ መስህቦችን በጥናት ለይቶ ለመመዝገብ እና 12 መስህቦችን ለመጠበቅ ታቅዶ፤ 32 የመመዝገብ እና 16 የመጠበቅ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የአለም አቀፍ ፕሮሞሽንና ግብይት ስራዎችን በማጎልበት የጎብኚዎች ፍሰትና የውጪ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ የሚረዱ የተለያዩ የፕሮሞሽንና የገጽታ ግንባታ ስራዎችንም በመስራት፤ በግማሽ የበጀት ዓመቱ 14,000 የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ክልሉን እንዲጎበኙ ተደርጓል።

የቱሪስት መረጃ ማዕከላት አገልግሎቶች ደረጃ እና የመረጃ ተደራሽነት የማሻሻል ስራ ጋር በተያያዘ፤ የቱሪስት መረጃ ማዕከላት ከማጠናከር በተጨማሪ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን ለተጠቃሚው ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡

የአገር ውስጥ ቱሪዝም ፕሮሞሽን ስራዎችን ከማሳደግ አንጻርም፤ በክልሉ በባለፈው ስድስት ወር በተሰሩ ስራዎች 6.3 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲጎበኙ በማድረግ፤ ከ382 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ በተመለከተ፡-

በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች በክልሉ መንግስት በኩል ጊዜያዊ እና ቋሚ ድጋፍ እየተሰጠ የሚገኝ መሆኑን ተናግረው፤ በቋሚነት የመልሶ ማቋቋም ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በተለይ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት ምክንያት የተፈናቀሉ እና የስጋት ቀጠና ውስጥ ያሉትን ለይቶ ከስጋት ነጻ በሆነ ቦታ ለማስፈር በተያዘው ዕቅድ መሠረት፤ በሶስት (3) ምዕራፍ የተከፈለ ውጤታማ ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን በሪፖርቱ አቅርበዋል፡፡

በመጀመሪያ ምዕራፍ የቅዲሚያ ቅዲሚያ የተለዩ 110 አባወራዎች በተገነባላቸው ቤት ከለሙሉ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው መኖር የጀመሩ ሲሆን፤ በሁለተኛ ምዕራፍ 406 ቤቶችን በመንግስትና በሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ለመገንባት ዝግጅት ተደርጎ 154 ቤቶች ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

 በሦስተኛ ምዕራፍም 318 መኖሪያ ቤቶችን በመንግስት እና በሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ለመገንባት ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ግንባታውን እስከ ሰኔ ወር በማጠናቀቅ ሙሉ በሙሉ በአካባቢው የተፈናቀሉ ዘጎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለው በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመገንባት ላይ መሆናቸውንና፤ የተወሰኑት ተጠናቀው  አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተናግረው፤ በቀጣይ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የድጋፍ ፓኬጆችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑን በዝርዝር ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቡትን የግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ተንተርሶ የምክር ቤት አባላት ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ በውይይቱ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የሚበረታታ ተግባራት መፈፀማቸውን በመግለፅ ለክልሉ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የክልሉ ምክር ቤት አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችንም አንስተዋል፡-

በተለይ የመንገድ፣ መብራት፣ የውሃ እና የጤና መሰረተ ልማት ችግሮች የተመለከቱ፣ የደምወዝ መዘግየት፣ ከነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ህገወጥነት፤ የትምህርት ጥራት ጉዳይ፤ ከፐብሊክ ሰርቪስ የሪፎርም ስራ ውጤታማነት ጋር የተያያዙና ሌሎች ጥያቄዎችን በማቅረብ ማብራርያ ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply