ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጌዴኦ ዞን ዲላና ገደብ ከተሞች ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የንፁሁ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን መርቀው በይፋ አገልግሎት አስጀመሩ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ለይፋዊ የልማት ስራዎች ጉብኝት በጌዴኦ ዞን ተገኝተው የተለያዩ የልማት ስረዎችን የጎበኙ ከመሆኑም ባሻገር በዞኑ ዲላና ገደብ ከተሞች የተገነቡ የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለጉብኝቱ ጌዴኦ ዞን፤ ዲላ ከተማ ሲደርሱ በክልሉና በጌዴኦ ዞን አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በዲሊ ከተማ ከ340 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑ ታውቋል።

በፕሮግራሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ለዘመናት የጌዴኦ ህዝብ ጥያቄ እንደነበር ገልፀው፤ ፕሮጀክቱ ታሪክን የቀየረ ነው ብለዋል።

የፓርቲው ከቃል እስከ ባህል ታሪካዊ ጉባኤ በተጠናቀቀ ማግስት ከተማዋ የሪጂኦ ፖሊስ ከተማነት ደረጃን አግኝታ ይሄን ግዙፍ ፕሮጀክት ለማስመረቅ መብቃቷ እጅግ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።

የንፁህ ውሃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክቱ የዲላ ከተማን ከፍ የሚያደርግ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከተማዋን ፅዱና ለነዋሪው ምቹ የሚያደርጋት እንደሆነም ገልፀዋል።

በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የመጠጥ የውሃ ፕሮጀክት ጠብቆ ተንከባክቦ በማቆየት ህብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገል እንዲችል የክልሉ መንግስት ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑንም በንግግራቸው አስረድተዋል።

በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢፌድሪ ውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና ለአመራሮች እንዲሁም ግንባታውን ላከናወነው ወገረት ኮንስትራክሽን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ ርዕሰ መስተዳድሩ እና ክቡር ሚንስትሩ በጌዴኦ ዞን የገደብ ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መርቀው በይፋ አገልገሎት አስጀምረዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ፕሮጀክቱ የገደብ ከተማን የውሃ ችግር የፈታ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ገልፀው፥ የውሃ ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ፍትሃዊ የንፁህ ውሃ ተጠቃሚነትንና ተደራሽነትን ለማስፋት የውሃ ተቋማት የማስተዳደር አቅም ማሳደግ በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግስት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በዘላቂነት ውሃ ለማግኝተት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ ተፈጥሮን መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በቡካላቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በክልሉ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን በተለያዩ ዞኖች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።  

የክልሉ የውሃና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ እና ሌሎች የበጀት አመራጮች በማፈላለግ በክልሉ 14 ከተሞችን ተደራሽ የሚያደርግ የውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልፀው፤ በዲላና ገደብ ከተሞች የተመረቁ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የዚሁ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ለዘመናት የጌዴኦ ህዝብ ጥያቄ እንደነበር ገልፀው ፕሮጀክቶቹ ለነበሩ ችግሮች ተገቢውን ምላሽ የሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።

Leave a Reply