
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ ጋር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ አምባሳደሩ እና ቡድናቸው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለይፋዊ የስራ ጉዳይ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ምስጋና አቅርበዋል፡፡



ኢትዮጵያ እና ቻይና ከግማሽ ምዕት አመት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነትና ትስስር ያላቸው መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የቻይና መንግስት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ሲደግፍ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የዚሁ አካል በርካታ የቻይና ካምፓኒዎች እና ቻይናዊያን በክልሉ በተለያዩ የልማትና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ በክልሉ የመንገድ እና የተለያዩ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አስትዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡



በቅርቡ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር በክልሉ ኢንቨስትመንትና ልማት ዙሪያ ውይይት በማድረግ የተለያዩ የልማት ትብብሮች ላይ ያተኮሩ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አስታውሰዋል።
ከዚህ ቀደም ከኢትዮ ቻይና የልማት ትብብር ጋር በተደረገው ስምምነት ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ወደ ቻይና የመላክ እና የማስተዋወቅ ስራዎች መጀመራቸውን አያይዘው ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ክልሉ በርካታ ፀጋዎች እና እምቅ የመልማት አቅም ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፤ የቻይና ባለሃብቶች በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡



በተለይ በማኑፋክቼሪንግ ኢንዱስትሪ፤ በአግሮ ፕሮሴሲንግ፤ በማይኒግ፤ በግብርና እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ልማት ድጋፍ እንዲያደርጉ የጠየቁት ርዕሰ መስተዳደድሩ፤ የክልሉ መንግስት በክልሉ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ የቻይና ባለሀብቶችን በእጅጉ የሚያበረታታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የቻይና ካምፓኒዎች በጥራት እና በብቃት ፕሮጀክቶችን በመጨረስ ለኢትዮጵያን ምሳሌ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የቻይና መንግስት በክልሉ በሰው ሀይል ልማት፤ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በኢንዱስቱሪው ዘርፍ እገዛ በማድረግ የክልሉን የልማትና የብልፅግና ራዕይ ስኬት እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡
ከዲጂታላይዜሽን ጋር በተያያዘም የክልሉን ስድስት ማዕከላት በሚያገናኙ የዲጆታል ቴክኖሎጂ የማስተሳሰርና የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ዝርጋታም መንግስታቸው እገዛ በያደርግ፤ የክልሉን አቅም እና አገልግሎት አሰጣጥ የሚያዘምንና የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው፤ በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት መኖሩን ጠቅሰው፤ ውይይቱና ትብብሩ ይህን ግኑኝነት በልማት ትብብሮች ይበልጥ በማጠናከር የክልሉንና የሀገሪቱን ልማት ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለው በቀጣይም የክልሉን ምርቶች ወደ ቻይና በመላክ የማስተዋወቅ ስራዎችን ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረው፤ ትብበሩን በባህል ልውውጦችና የኢኮኖሚ ትስስሮች ለማጠናከር የሚሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ እና አምባሳደሩ ከውይይቱ በተጨማሪ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተከበረ የቻይና የባህል ቀን የታደሙ ሲሆን፤ ቀኑ በዩኒቨርስቲው መከበሩ የቻይናውያንን ባህል ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ከማስተዋወቅ ባሻገር ለምርምር ስራዎች የሚያግዝ መሆኑ ተጠቁሟል።






በመርሃ ግብሩ የቻይናውያንን ባህል የሚገልፁ የተለያዩ ቁሳቁሶችና የስነ ፅሁፍ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
አምባሳደሩ እና ሉዕካቸው በቆይታቸው ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት ለአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። ከህክምና ቁሳቁስ ድጋፉ በተጨማሪ ከቻይና የመጣ የክምና ቡድን በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።







ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ሆስፒታሉ ከተመሰረተ የቆየ ቢሆንም ከሚያስተናግደው የሰው ቁጥር አንፃር ብዙ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልፀል፤ ለአምባሳደር ቸን ሃይ እና ለቻይና የህክምና ቡድን ለተደረገው ድጋፍ በራሳቸውና በክልሉ ህዝብ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።