
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት በማስገባት ለአገልግሎት ማዋል በሚቻልበት አግባበብ ዙሪያ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ቻይና ከግማሽ ምዕት አመት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የቻይና መንግስት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ሲደግፍ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ድጋፍ አካል የክልሉ መንግስት ከዚህ ቀደም ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር በክልሉ ኢንቨስትመንት፤ በገበያ ትስስር እንዲሁም በገጠር አማራጭ የኢነርጂ የኃይል አቅርቦት ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት በማድረግ ውጤታማ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠሩን አስታውሰዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት በክልሉ ዘመኑን የዋጀ፤ ወጪ ቆጣቢና አስተማማኝ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በማለም የኤሌክትሪክ መኪኖችን በስፋት በማስገባት ለአገልግሎት ለማዋል ማቀዱን ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በሚቀጥሉት አምስት አመታት እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን የትራንስፖርት አገልግሎት በኤሌክትሪክ መኪኖች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ለዕቅዱ ውጤታማ አፈጻጸም ከኮሚቴው ጋር ያለውን የትብብር ማዕቀፍ በማስፋት አብሮ ለመስራት ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡


ለዕቅዱ ተግባራዊነት የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት፤ የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፤ በቂ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሞያዎች፤ መኪኖችን ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች የሚፈልግ መሆኑን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ከኮሚቴው ጋር በጆይንት ቨንቼር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ክልሉ ለኤለክትሪክ መኪኖች አስፈላጊ አገልግሎቶችን ዘለቀታዊ በሆነ መንገድ በራሱ መሰጠት እንዲችል፤ ኮሚቴው በቻይና የሚገኙ ቴክኒካል ኮሌጆች በሰው ሃይል ስልጠናና በተለያዩ የቴክኒካል ድጋፎች ዙሪያ በክልሉ ከሚገኙ የቴክኒክና ሞያ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩበትን አግባብ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የክልሉን ዕድገት በማገዝ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ ኮሚቴው የክልሉን የይርጋ ጨፈ ብራንድ ቡና በቻይና ገበያ በማስተዋወቅ ውጤታማ የገበያ ትስስር በመፍጠሩ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱ በበኩላቸው፤ በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የልማት ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልፀው፤ ይህም በኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽንና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ጉልህ አስትዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሊቀ መንበራ የክልሉ መንግስት ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ለማሳደግ ላሳየው ፍላጎት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ኮሚቴው በክልሉ ለታቀደው የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይ በሰው ሃይል ስልጠና፤ በቴክኒካል ድጋፍ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በቻይና የሚገኘው የሺዥጁንግ ቴክኒሺያን ኮሌጅ (Shijazhuang Technician College) በክልሊ ከሚገኙ የቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች ጋር በትብብር እንዲሰራ ኮሚቴው የሚያመቻች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም በቅርቡ ከኮሌጁ የሚመጣ ሉዑክ በክልሉ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ለዕቅዱ ተግባራዊነት በዝርዝር ተወያይቶ ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ኮሚቴው በኤሌክትሪክ መኮኖች ዙሪያ ከክልሉ መንግስት ጋር አብሮ ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡