
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት “ቃልን ወደ ባህል፤ ፀጋን ወደ ገቢ” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የተዘጋጀ ክልላዊ የታክስ ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ክልሉ በዕቅድ ባስቀመጠው ልክ ገቢ መሰብሰብ ባለመቻሉ የበጀት ጉድለት ዉስጥ ይገኛል ያሉ ሲሆን፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።



በክልሉ አሁንም በመቀጠር ከሚገኝ ገቢ በስተቀር ከንግድ፣ ቤት ኪራይ፣ የገጠር መሬት መጠቀሚያ መሰል ዘርፎች የሚሰበሰበው ግብር አነስተኛ መሆኑንም ጠቅሰው፥ የገቢ ምንጩን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ልማት ላይ ማዋል የህልውና ጉዳይ ነዉ ያሉ ሲሆን፤ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የሚስተዋለው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለማለቅ እና ደምወዝ በጊዜ መክፍል ያለመቻል ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ አለመቻል መሆኑን በአጽንኦት ገልፀዋል።



ገቢ በታቀደው ልክ አለመሰብሰቡ ግብር ሰብሳቢ አመራሩ እና ባለሙያው በቁርጠኝነት አለመፈፀም እና የገቢ አሰባሰብ ሥራዉ በጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ባለመደገፉ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ለልማት ማዋል እንደሚገባም አሳስበው፥ ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ የህዝብ እንዴራሴዎችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ገልፀዋል።
ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕያችን በሙላት ሊሳካ የሚችለው ገቢን በአግባቡ ሰብስቦ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለልማት ማዋል ሲቻል መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል።
ለዚህ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን እና የዲጅታል አሰራርን ተደራሽ በማድረግ የገቢ አሰባሰብ ስራን ከማሳደግ ባለፈ የገቢ ምንጮችንና አማራጮችን ማስፋት ቁልፍ ነው ብለዋል።






አመራሩና ባለሞያው ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በክልሉ ተቋማዊ የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት፤ ሶስቱን የሪጅዮፖሊስ ከተሞች (ወላይታ ሶዶ፤ አርባ ምንጭ እና ዲላ) ‘ስማርት’ ወደ ሆነ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት እንዲገቡ አንደሚደረግም አስታውቀዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው፥ መድረኩ መሪዉ ብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባዔውን በማድረግ በገቢዉ ዘርፍ አቅጣጫ ባስቀመጠ ማግስት የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ ነባር አቅሞችን የሚያዳብር፣ ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚያሻግር ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ ማድረጉንም አውሰተዋል፡፡
በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ውጤታማነትን ለማሳደግና የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም በርካታ ተግባራት እንደሚቀሩ ተናግረው፥ በቀጣይ የተቀናጀ ርብርብ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ቢሆንም የገቢ መሰረቱን በማስፋትና ግብይትን በደረሰኝ በመፈፀም በኩል ችግሮች እንዳሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ከአቅም በታች ገቢ መሰብሰብ፣ ዉስን የማዘጋጃ ቤት ገቢ ላይ ትኩረት ማድረግ፣ የገቢ አሰባሰቡን በቴክኖሎጂ አለማዘመን፣ ማጭበርበርን እንደ ባህል የያዙና ከነጋዴ ጋር የሚተባበሩ ባለሙያዎች መኖር፣ የመንግስትና ፓርቲ መዋቅር የሚመሩ አካላት የገቢ አፈፃፀምን አለመደገፍና በዝርዝር አለመገምገም እንደ ችግር ተነስቷል።






በሌላ በኩል በክልሉ የተዘጋጀው የገጠር መሬት መጠቀሚያ አዋጅ እና የኢንቨስትመንት ግብር ላይ የተደረገው ማሻሻያ ተጨማሪ የገቢ አቅም እንደሚፈጥር በመድረኩ ተገልጿል።
ክልላዊ የታክስ ንቅናቄ መድረኩ ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በገቢው ዘርፍ ሊከናወኑ የሚገባቸው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡