
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል፡፡
በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ፤ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት አመት የግማሽ አመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው የክልሉ መንግስት በግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ውጤታማ በሆነ አግባብ ማከናወኑን ግለፀዋል፡፡
በተለይ በዋና ዋና የልማት አውታሮች በተሰሩ ስራዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር ይበልጥ የሚያጎለብቱ እና ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይን ባጠረ ጊዜ ለማሳካት መሰረት የጣሉ ስኬቶች መመዘገባቸውን በሪፖርታቸው በስፋት መዳሰስ ችለዋል፡፡



እንደዚሁ ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት መነሾ፤ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ሰፊ ውይይት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
በጉባኤው በሁለተኛ ቀን ዉሎዉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፡-
የክልሉ መንግስት ከክልሉ ምስረታ ማግስት ጀምሮ ሰላምና ፀጥታን ዋነኛ ቀዳሚ አጀንዳው በማድረግ፤ ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት የማድረግ ግብ ጥሎ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው ክልሉ አንፃራዊ ሰላም የተረጋገጠበት በመሆኑ የተለያዩ ሀገራዊ መርሃ ግብሮች የሚካሄዱበት ተመራጭ ክልል መሆኑን ገልፀዋል።
ለአብነትም በክልሉ አዘጋጅነት የተካሄደው 19ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እንዲሁም በቅርቡ የተጠናቀቀው የታዳጊ ወጣቶች ሀገር አቀፍ የምዘና ዉድድርን ጠቅሰዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ከምንም በላይ ከከፋፋይ አጀንዳ ተጠብቀን የውስጥ ሰላም ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም የፀጥታ መዋቅሩን የሚያጠናክሩ የሪፎርም ስራዎችን ጨምሮ ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረጉ የሰላምና ፀጥታ ስራዎች በትኩረት መሰራታቸውን ተናግረዋል።



በኮንሶ፣ አሌ፣ ጋርዱላ፥ ቡርጂ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ላይ ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ አካላትን የሀገር ሽማግሌዎች በአመራሩ ብርቱ ጥረት በማስቆም አንፃራዊ ሰላም መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚታዩ አለመግባባቶችን ውስጣዊ ችግሮችን በመፍታት የግጭት ነጋዴዎችን በማጋላጥ በአቋም መሄድ ያስፈልጋልም ብለዋል።
በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ከህብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎችን በማጠናከር እንዲሁም ከተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት በተለይም ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሀይማኖት ተቋማት ጋር ፎረም ፈጥሮ መሰራቱ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ለማረጋገጥ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡
ይህም በመሆኑ የተለያዩ ሀገራዊ መርሃ ግብሮች የሚካሄዱበት ተመራጭ ክልል ሊሆን ችሏል ብለዋል። በክልሉ አዘጋጅነት የተካሄደው 19ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እንዲሁም በቅርቡ የተጠናቀቀው የታዳጊ ወጣቶች ሀገር አቀፍ የምዘና ዉድድርን ለማሳያ ጠቅሰዋል።
ክልሉ ከአጎራባች አገራት፤ ከአዋሳኝ ክልሎችና ዞኖች ጋር በቀጠናዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ጠንካራ የስራ ግንኙነት በመፍጠር የጋራ ጥረት ማድረጉን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም በቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
ለቀጠናው ሰላምና ፀጥታ በዋናነት የሴራ ፖለቲካ፣ የህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ኮንተሮባንድ ስጋት መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ በቀጣይም የማያዳግም ዕርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።



በተለያዩ አካባቢዎች ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ በመስራት የተቀናጀ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
አክለው የክልሉ ህዝቦች ነባር ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓቶችና የሰላም ግንባታ ተቋማት ባለቤት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሰት እኚህን በክልሉ ያሉ ማህበራዊ ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማጽናት በቀጣይም የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህግ የበላይነትን በሁሉም አካባቢዎች በማረጋገጥ እና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራቱን በማጠናከር ክልሉን የሰላም ተምሳሌት የማድረግ ትልም ዕውን የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን በማብራሪያቸው ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከፋይናንስ ዕጥረት እና ከውስጥ ገቢ አኳያ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፡- ህገ ወጥ ቅጥር፣ በወረዳዎች የሚገኝ የተለጠጠ ወዋቅርና የአመራር ብዛት እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪዎች ለፋይናንስ ዕጥረቱ ዋነኛ ምክንያት ናቸው ያሉ ሲሆን፤ የውጪ ፍላጎት የናረበት ምክንያት ምንድ ነው የሚለውን ቆም ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዕጥረቱን ለማቃለል ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ ፍትሀዊ ግብርን በአግባቡ በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን ለማጎልበት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለው በውስጥ ገቢ ወጪያችንን መሸፈን እና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ማድረግ ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልፀዋል።
በተያያዘ የአንዳንድ ፕሮጀክቶች መዘግየት ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በምላሻቸው ከዳሰሱዋቸው ጉዳዮች መካከል ከመሰረተ ልማት እና ከተቋማት አገልግሎትና ተደራሽት ጋር የተያያዘ ይገኝበታል፡፡



የክልሉ መንግስት ከተቋማት አገልግሎት እና ተደራሽነት ጋር በተያያዘ በየደረጃው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም ከፌዴራል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በርካታ የገጠር ቀበሌያት የመብራት አገልግሎት በማግኘት ላይ አለመሆናቸውን ገልፀዉ፤ ከመብራትና ቴሌኮም ጋር ተያይዞ ከተደራሽነት አኳያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እና ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለመፍታት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንገድ መሰረተ ልማትን በተመለከተ አካባቢን መንከባከብ መንገዶች እንዳይበላሹ መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መሰራት ባለባቸው መንገዶች ዙሪያ ለፌደራል ጥያቄ ቀርቦ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ጥያቄዎች እንዳሉ ሁሉ፤ ያሉትን የመሠረተ-ልማት አውታሮችን የመንከበካብና የመጠበቅ ተግባር ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው ከትምህርት ቤት ግንባታ ጋር በተገናኘ አርብቶ አደሩ አከባቢ ትኩረት በመስጠት የሚስተዋሉ የማስፈፀም ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።



የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ማስቆም፣ በየአካባቢው በኢንቨስትመንት ስም ታጥረዉ ያሉ መሬቶችን ወደ ልማት ማስገባት፣ በተለያዩ አከባቢዎች ያሉ የአገልግሎት አሠጣጥ ችግሮችን ማሻሻል፣ ከጤና መድህን አገልግሎት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን መፍታት ርዕሰ መስተዳድሩ አፅንኦት ከሰጧቸዉ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸዉ።
አክለው “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መርህ ተግባራትን ለማከናወን በተገባው ቃል መሠረት የንቅናቄ ስራዎችን ባህል በማድረግ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በጉባኤው ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሩ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አባላት ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከተሰጡ ምላሾች መካከል፦

ከስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ሥራ ጋር በተያያዘ ሥራው በአንድ ተቋም ብቻ የሚሰራና የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ በየደረጃው በሚገኙ አካላት መደገፍ አለበት ብለዋል። ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የተቀመጡ አቅጣጫዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ጌዴኦ እና ጋሞ ዞኖች በተወሰነ መልኩ አቅጣጫውን ተግባራዊ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።
ከብድር ስርጭት ጋር በተያያዘ በተወሰነ መልኩ እየተሰራጨ ቢሆንም የቁጠባዉ መጠን ግን ለማሰራጨት የሚበቃ አይደለም የተባለ ሲሆን፤ የፖለቲካ አመራሩ በከፍተኛ ትኩረት ሊመራዉ እንደሚገባ ተጠቅሷል።

ትምህርትን በተመለከተ በተሰጠው ምላሽ፤ የትምህርት ልማት ሥራ ቀጣይነት ባለዉ መልኩ ባህል አድርጎ መስራት በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ጭምር ትኩረት የተሰጠው መሆኑ ተገልጿል።
አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን እየተሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን፤ አዲሱ ካሪኩለም በትምህርቱ ዘርፍ ያጋጠመውን ችግር በማረም በኩል ዉጤት እያመጣ ባቻ ሳይሆን ሀገርን ወደ ብልጽግና የሚያሻግር ትዉልድ በመቅረጽ ላይ ነው ተብሏል፡፡
በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የሆኑበትና በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የተጀመረው የአንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ ኢንሼቲቭ መፅሐፍትን ለተማሪዎች ተደራሽ በማድረግ በኩል ከፍተኛ እገዛ ማድረጉም ተወስቷል።
ከተማሪዎች ምገባ ጋር ተያያዞ፤ ማህበረሰብ ተኮር የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም እየተካሄደ የሚገኘው በክልሉ መንግስት እና በአጋር አካላት ድጋፍ ነዉ የተባለ ሲሆን፤ ወደ ወረዳዎች እንዲወርድ የተቀመጠው አቅጣጫ በሚፈለገው መልክ ተፈፃሚ መሆን አልቻለም፤ ለዚህም ተጨማሪ ስራ ይፈልጋል ተብሏል።

ከመጠጥ ውሃ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በ 14 ከተሞች የዉሃ ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ነዉ። በዚህም ከ 1 ሚሊዮን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በተጨማሪም የሳዉላ፣ ዲላና ገደብ የዉሃ ፕሮጀክቶች ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረዋል የተባለ ሲሆን፤ የሻንቶናና ዘፍኔ ከተሞች የዉሃ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጠናቀቁም ተገልጿል።
ብልጽግና ፓርቲ የጀመረውን የሚጨርስ ፓርቲ ነዉ። በዚህ ረገድ ካፒታል ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን፤ የሶዶ፣ አርባምንጭ፣ ጊዶሌ እና ዲላ ማረሚያ ተቋማት ግንባታን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሌላ ነኩል የጥሬ ገንዘብ እጥረት ከገቢ አሰባሰባችን ጋር የሚገናኝ ነዉ የተባለ ሲሆን፤ ገቢን አሟጦ ያለመሰብሰብ ችግር መኖሩ ተገልጿል። ከተሞች የሚሰበስቡትን ገቢ ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው ነዉ የሚያዉሉት። ይህ ገቢ አሰባሰብን የሚያሳድግ ነዉ። ደመወዝን በተመለከተ ክልሉ እራሱጋ የሚያስቀረው ምንም አይነት ገንዘብ ባለመኖሩ በተቀየሱ የመፍትሔ መንገዶች ችግሩን ለመቅረፍ ይሰራል ተብሏል፡፡
የክልሉን የምርጥ ዘር ፍላጎት እስከ 2018 ድረስ 50% ለመሸፈን፣ በ 2019 ግን ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑ የተነገ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት ከቀድሞ የተሻለ የምርጥ ዘር መያዝ መቻሉ ተገልጿል።
ከግብርና ጋር ተያይዞ በክልሉ 135 ሺህ ሄ/ር የእርሻ መሬት በመስኖ ለምቷል የተባለ ሲሆን፤ አሁን ያለው የመስኖ አቅም ከ 140 ሺህ ሄ/ር በላይ የማያለማ በመሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አስፈላጊ መሆኑም ተጠቅሷል።

እስከ ታህሳስ 30 ድረስ የሌማት ትሩፋት የመንደር አደረጃጀትን ለማጠናቀቅ በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በሁሉም ዞኖች 10 ሺ 817 መንደሮችን ማደራጀት ተችሏል ተብሏል።
በክልሉ ዘንቲ፣ ሰርማሌ እና በዴሳን ጨምሮ የአራት ትላልቅ ድልድዮች ግንባታ ተጠናቋል። በተያዘው ዓመት ስድስት ትላልቅ ድልድዮች ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው የሚጠናቀቅ መሆኑም በምላሾቹ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በርዕሰ መሰተዳድሩ በቀረበው የክልሉ መንግስት የግማሽ ዓመት ሪፖርት በስፋት በመወያያት እና ለተነሱ ጥያቄዎችም በቂ ምላሽ መሰጠቱን በማጠን ሪፖርቱን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።