ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ እና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የወላይታ ሶዶ የኢቢሲ ተጨማሪ የይዘት ምንጭ ስቱዲዮን በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ገለልተኛ፤ ኢትዮጵያን የሚመስል የሚዲያ ተቋም ለመገንባት ባደረገው ሪፎርም መሰረት፤ የኢቢሲ የይዘት አድማስን በማስፋት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ሚዲያ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር፤ ለሀገራዊ መግባባት፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትስስርን ለማጎልበት፤ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ፤ ለባህልና ቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት እና ሌሎችም ያለው ሚና ዘርፈ ብዙና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ረገድ፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በክልሉ በወላይታ ሶዶ ከተማ የገነባው የኢቢሲ ቅርንጫፍ ስትዲዮ፤ በቀጣይ በክልሉ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ጎልህ ሚና ይጫወታል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ብዝኀ ማንነትና ባህል ያላቸው 32 ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተዋደው እና ተከባብረው የሚኖሩበት መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ የኢቢሲ ወላይታ ሶዶ ስትዲዮ በአጭር ጊዜ ስራው ተጠናቆ ወደ ስራ መግባቱ ያሉንን የአብሮነት ማህበራዊ ዕሴቶች ለማጎልበት የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
በነጠላ ትርክት እርስ በእርስ የተጋመደና የቱባ እሴቶች ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለመነጣጠል የሚሞክሩ አካላት አሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ነጠላ ትርክት ፈጥረው ህዝብን ሊነጣጥሉ የሚፈልጉ አካላትን በአብሮነት መታገል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ እነዚህን አካላት ለመታገል ኢቢሲ በወላይታ ሶዶ ከተማ የገነባው ስቱዲዮ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።
እውነተኛ መረጃን ለህዝቡ በማድረስ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ ስቱዲዮውን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ በግብርና እና ቱሪዝም ዘርፍ ክልሉን ወደ ባለፀጋነት መቀየር የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው መሆኑንን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ሚዲያው በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን ለአለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረው፤ በዚህ ረገድ ኢቢስ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ ለጠላት በር ላለመክፈት አንዳችን ለአንዳችን ከመቆም ባለፈ ተባብረን መስራት አለብን ብለዋል።
በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን ህብረታቸውን በማጠናከር በጋራ ሊቆሙ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል። አንድ ሆነን ከተባበርንና ከተጋገዝን ማንም ሊነካን አይችልም ሲሉም አክለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ አገራዊ ብልጽግና ማምጣት የሚቻለው የኢኮኖሚ ልዕልናን በማረጋገጥ ተረጂነትን የሚጸየፍ ማህበረሰብ ማፍራት ሲቻል ነው።
የወላይታ ሶዶ ኢቢሲ ስቱዲዮ በክልሉ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህላዊ እሴቶች እና የክልሉን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ የሚሰራበት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። ስቱዲዮው ብልጽግናን የሚናፍቅና ተረጂነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት መሳሪያ መሆኑንም አክለዋል።
የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፣ ኢቢሲ በሁሉም አካባቢዎች ተገኝቶ ዘገባዎችን በመስራት በአፍሪካ ደረጃም እንደ ህዝብ ለመደመጥ በሚሰራው ስራ አመራሩ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የወላይታ ሶዶ ኢቢሲ ስትዲዮ በአጭር ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ላደረጉት ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ ከኮርፖሬሽኑ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በስቱዲዮ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፣ የብልፅግና ፓርቲ ህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ እና የኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡